በትግራይ የብሄሮች ፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል በድምቀት እንደሚከበር ተገለጸ

54
መቀሌ ኢዜአ ህዳር 22/2012 በትግራይ ክልል የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በድምቀት ለማክበር ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ገለጹ። አፈ ጉባኤው አቶ ሩፋኤል ሽፈረ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ  "በዓሉ በክልሉ ህገ መንግሰታዊ ስርዓታችን ለዘላቂ ሰላምና ጥቅም በሚል መሪ ሀሳብ ህዳር 29 ይከበራል" ብለዋል፡፡ በዓሉ የሚከበረው  በክልሉ  ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ  ልማት ስራዎች በሚያሳይና በስፖርታዊ ውድድር ነው። ለ14ኛ ጊዜ ዘንድሮ በዓሉ ሲከበር ህገ መንግስቱና የፌዴራል ስርዓቱ ከተጋረጠበት አደጋ ለማዳን ጭምር መሆን እንዳለበት አመልክተዋል። በሀገር አቀፍ ደረጃ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አዘጋጅነት በአዲስ አበባ በሚከበረው በዓልም ክልሉ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች  እንደሚሳተፍም አስታውቀዋል፡፡ በዓሉ የሚከበርበት ዋና ምክንያት  ባለፉት ዓመታት ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች  ባህላቸው ፣ቋንቋቸውና እምነታቸው በነጻነት እንዲራምዱ ህገ መንግስቱና ፌደራል ስርዓቱ የጎላ አስተዋጽኦ በማድረጉ እንደሆነ አፈ ጉባኤዋ ተናግረዋል፡፡ የምጣኔ ሀብት እድገቱ ቀጣይነት እንዲኖረውና የህዝቡ ተጠቃሚነት እንዲጎለብት ህገ መንግስቱና የፌደራል ስርዓቱ  ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አስረድተዋል፡፡ አሁን በህገ መንግስቱ የተረጋገጡት መብቶች ወደ ኋላ የሚመልሱ ምልክቶች እየታዩ መሆናቸውን ገልጸዋል። "የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችን  ወደ ዳግም ጭቆና የሚመልስ ተግባር ህገ መንግስቱን የሚቃረን በመሆኑ ህዝቦች አሁንም በጋራ ሊታገሉ ይገባል "ብለዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም