በኦሮሚያ ለሚከበረው የብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ዝግጅት እየተደረገ ነው---የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ

38

ኢዜአ ህዳር 22/2012 በኦሮሚያ ክልል አስተናጋጅነት ዘንድሮ ለ14ኛ ጊዜ ለሚከበረው የብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል በቂ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሎሚ በዶ ገለጹ።

አፈ ጉባኤዋ “ህገ መንግስታችን ለሀገራችን ዘላቂ ሰላም በሚል መሪ ሀሳብ ህዳር 29 ለሚከበረው በዓል ዝግጅት አስመልክተው ዛሬ በአዳማ ከተማ አባ ገዳ አደራሽ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸው እንዳሉት በዓሉ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የራሳቸውን ባህልና ማንነት የሚያሳውቁበት ከመሆኑም ባለፈ መልካም ግንኙነትን ለማጠናከር ወሳኝ ሚና አለው።

ሀገሪቱ ወሳኝ የለውጥና የሽግግር ምዕራፍ ላይ ባለችበት ወቅት በዓሉ መከበሩ የዘንድሮው ልዩ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።

በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር የክልሉ መንግስት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቂ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አፈ ጉባኤዋ አስታውቀዋል።

“የክልሉን ታሪካዊና የቱሪዝም መስህቦች የማስተዋወቅ ፣ የኦሮሞ ህዝብ ለዓለም ማህበረሰብ ያበረከተው የገዳ ሥርዓትና የህዝቡ አቃፊነት በተለያዩ ሲምፖዚየሞችና መድረኮች ለታዳሚዎች ከነገ ጀምሮ ይቀርባል “ብለዋል።

የበዓሉን አከባበር የተሳካ ለማድረግ ከኦሮሚያ አጎራባች ክልሎችና የፀጥታ አካላት ጋር ውይይት መደረጉን ያመለከቱት አፈጉባኤዋ የበዓሉ ታዳሚዎች አልፈው በሚመጡበቸው የኦሮሚያ ከተሞች አቀባበል እንደሚደረግላቸው ገልጸዋል።

በዚህም የኦሮሞ ህዝብ ባህል፣ እንግዳ ተቀባይነትና አቃፊነት በተግባር የሚያሳዩ ክዋኔዎች እንደሚፈሙም አስረድተዋል።

እንደአፈ ጉባኤዋ ገለጻ  የፌዴራል ፣የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ክልል የፀጥታ አካላት በትብብር እየሰሩ ነው፤ የበዓሉ ታዳሚዎችም ሆኑ ህብረሰተቡን ስጋት ላይ የሚጥል ምንም ዓይነት ክፍተት እንዳይፈጠር ትኩረት ተሰጥቷል።

እንግዶችን በሁሉም የአዲስ አበባ መግቢያ በሮችና የፊንፍኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች ደማቅ አቀባበል ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ነው።

“ከነገ ጀምሮ እስከ በዓሉ ዋዜማ የተለያየ ሲምፖዚየሞችና ባዛሮች በአዲስ አበባ የኦሮሞ የባህል ማዕከልና በኦሮሚያ ከተሞች ይከፈታሉ “ብለዋል።

በበዓሉ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተወካዮችና እንግዶች ጨምሮ 35ሺህ የሚጠጉ ሰዎች እንደሚታደሙ ይጠበቃል።

የዘንድሮው 14ኛው የብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል በኦሮሚያ ክልል አስተናጋጅነት ህዳር 29/2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚከበር ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም