አፍሪካ ለህዋ ሳይንስና ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት ትኩረት እንድትሰጥ ተጠየቀ

69

ኢዜአ ህዳር 22 / 2012 ለአፍሪካ ዘላቂ ምጣኔ ሃብት ዕድገት የህዋ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ያለውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ ለዘርፉ መሰረተ ልማት ትኩረት እንዲሰጥ ተጠየቀ።

የአፍሪካ አገሮች በምጣኔ ሃብትና ማህበራዊ ዘርፎች እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ለህዋ ቴክኖሎጂ የሰጡትን ትኩረት የሚዳስሰው ስምንተኛው የአፍሪካ የህዋ ሳይንስና ቴክኖሎጂ አመራር ስብሰባ ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀምሯል።

የአፍሪካ አገሮች በህዋ ሳይንስና ቴክኖሎጂ መዋዕለ-ነዋያቸውን በማፍሰስ ዘርፉን ለማበልጸግ የሰጡት ትኩረት አነስተኛ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የሰው ሃብት ልማት፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር ዶክተር ማሃማ ኦድራኦጎ የህዋ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ለአፍሪካ ምጣኔ ሃብት እድገት ያለውን ጠቀሜታ አንስተዋል።

አፍሪካ ዘርፉን በተቀናጀ መንገድ ባለመምራትና በግንዛቤ አለማደግ የሚያስገኘውን ጠቀሜታ እያጣች ነው ብለዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ለህዋ ሳይንስ ሰው ሃብት ልማት፣ ተቋማት ግንባታ፣ ጥናትና ምርምር፣ በመንግስትና በግሉ ዘርፍ ያለውን ትብብር በማጠናከር መጠቀም ያስፈልጋል።

ለህዋ ሳይንስ የሚያስፈልጉ መሰረተ ልማቶችን በማሟላት ምቹ አካባቢን ፈጥሮ ለአፍሪካ ዘላቂ ልማት ዘርፉ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ማሳደግም እንዲሁ።

የኢትዮጵያ ህዋ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን በላይ አፍሪካ ዘላቂ የህዋ ኢንዱስትሪን በማልማት ጥቅም ላይ ለማዋል ጠንካራ ሰራ ያስፈልጋታል ብለዋል።

በአፍሪካ አገሮች መካከል ተባብሮ አለመስራት፣ የግንዛቤ እጥረት፣ ግልጽ የህዋ ፖሊሲና ስትራቴጂ አለመኖና የመሪዎች የቁርጠኝነት ማነስ ዘርፉን እያጋጠሙ ካሉ ችግሮች መካከል ናቸው።

አህጉሪቱን በህዋ ሳይንስ ተወዳዳሪ ለማድረግ የዘርፉ ምሁራን፣ ዓለም አቀፍ የአስትሮኖሚ ማህበርና ሌሎች በዘርፉ ላይ የሚሰሩ ተቋማት ሙያዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያ ዘርፉን በማልማት በምጣኔ ሃብት ዕድገት ያለውን አስተዋጽኦ ለመጨመር እየሰራች መሆኑን ገልጸው ከሌሎች የአፍሪካና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር መስራቷን አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ በበኩላቸው የበለጸጉ አገሮች መሪዎች ለህዋ ሳይንስ በሰጡት ትኩረት የህዋ ሳይንስንና ቴክኖሎጂን በምጣኔ ሃብት ዕድገታቸው በተራቀቀ ሁኔታ እንዲጠቀሙት አስችሏቸዋል ብለዋል።

የአፍሪካ አገሮች ለዘርፉ ልማት የሚፈለገውን ያህል መዋዕለ-ነዋይ እያፈሰሱ አለመሆኑን እንደ ችግር አንስተዋል።

በመሆኑም ለአፍሪካ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት የህዋ ሳይንስን ለመጠቀም አገሮች ለዘርፉ የሚይዙትን በጀት እንዲያሳድጉ ጠይቀዋል።

"የህዋ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ለዘላቂ ልማት" በሚል እየተካሄደ የሚገኘው ይህ ስብሰባ የአፍሪካ ስፔስ ተስፋና ፈተናዎች ላይ ያጠነጥናል።

በዘርፉ የተደረጉ ጥናትና ምርምሮች፣ በአፍሪካ የህዋ ሳይንስ ዕድገት ግምገማ፣ የህዋ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂዎችና አተገባበራቸው ለሶስት ቀናት የሚቆየው ስብሰባ ዋና ትኩረት ከተባሉ ነጥቦች ውስጥ ይጠቀሳሉ።

የአፍሪካ የህዋ ሳይንስና ቴክኖሎጂ አመራር ስብሰባ መካሄድ የጀመረው እንደ ጎርጎሮሳውያን አቆጣጠር በ2005 ሲሆን ባለፈው አመት በናይጀሪያ ተደርጓል።

ስብሰባው አፍሪካ በህዋ ሳይንስ እያከናወነች ያለውን ተግባር በመገምገም ያሉ አማራጮችና ፈተናዎችን በመለየት ለመሪዎች ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም