የሶማሌ ክልል ነዋሪዎች ለህዳሴው ግድብ ድጋፋቸው ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገለጸ

60
ኢዜአ ህዳር 22/2012  የሶማሌ ክልል ነዋሪዎች ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርጉት ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ገለጹ። ላለፉት ሁለት ዓመታት በሶማሌ ክልል ቆይታ ያደረገው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ዋንጫ የሽኝት ስነ ስርዓት ዛሬ በጅግጅጋ ከተማ ተካሄዷል። የሽኝት ስነሰርዓቱን ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀው ፓናል ውይይት ወቅት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አደን ፋራህ እንዳሉት ግድቡን አስመልክቶ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው በኩልም በጋራ የማልማት እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት መርህ ተከትላ ውጤታማ ስራ እያከናወነች ነው። ግድቡ በመላ ሀገሪቱ የኃይል እጥረት ችግር እንደሚፋታ አመልክተው የክልሉ ነዋሪዎች እንደሌላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ የግንባታውን ሂደት ሲደግፍ መቆየቱን ገልጸዋል። ግንባታው እስኪጠናቀቅ ድረስ በቦንድ ግዥ፣ በድጋፍ እና በችግኝ ተከላ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራው እስከ ወረዳ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል። በክልሉ የቦንድ ሽያጭ መቀጠሉን ጠቁመው ህዝቡ የሀገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦች የጋራ አሻራ ላረፈበት ለታላቁ ህዳሴ ግድብ የሚያደርገው ሁለንተናዊ ተሳትፎ እንዲቀጥልበትም ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ ጥሪ አቅርበዋል። የሶማሌ ክልል ነዋሪዎች ከ2004 እስከ 2011 ዓ.ም ድረስ 356 ሚሊየን ብር ለግድቡ ድጋፍ ማድረጋቸውን  የገለጹት ደግሞ በክልሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዲቀነ ጣሂር ናቸው። የህዳሴው ግደብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረስላሴ በበኩላቸው እስካሁን የግድብ ግንባታው አፈፃፀም 69 ነጥብ 9 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል። “ ለግንባታው 99 ቢሊየን ብር ወጭ ሆኗል “ ያሉት ዳይሬክተሯ ከዚህ ውስጥም ህዝቡ ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ አስተዋጽኦ ማድረጉን ተናግረዋል። "ግድቡ የልማትና የታሪክ አሻራን አንድ ላይ የሚያስተሳሰር ነው" ያሉት ወይዘሮ ሮማን እስካሁን 282 ሺህ በላይ ሰራተኞች እና የሰቪክ ማህበራት አባላት ግድቡን መጎብኘታቸውን አውስተዋል። የፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች ለግድቡ የሚያደርጉት ድጋፍና ተሳትፎ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል ። ከፓናል ውይይቱ በተጨማሪ  በጅግጅጋ ከተማ ከአምስት ሺህ በላይ ሰዎች የተሳተፉበት የሩጫ ውድድር ተካሄዳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም