ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉን ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩቶች ማህበር ጉባኤ ታስተናግዳለች

61
ኢዜአ እዳር 22/2012 ኢትዮጵያ የዘንድሮውን ዓለም አቀፍ የህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩቶች ማህበር ጉባኤ ለማስተናገድ የሚያስችላትን ዝግጅት ማጠናቀቋን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት አስታወቀ፡፡ የዓለም ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩቶች ማህበር የ13ኛው ጉባኤ "ለድንበር ተሻጋሪ የህብረተሰብ ጤና ችግሮች በመረጃ የበለጸገ ዓለም አቀፍ እርምጃ" በሚል መሪ ሃሳብ  ከነገ ህዳር 23 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለአራት ተከታታይ ቀናት በአዲስ አበባ ይካሄዳል። በጉባኤው ላይ ከ95 በላይ በሆኑ አገራት የሚገኙ የህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩቶች ይሳተፉሉ። ኢትዮጵያ ጉባኤውን እንድታዘጋጅ የተመረጠችው ባለፈው ዓመት በእንግሊዝ ለንደን በተካሄደው 12ኛው የዓለም ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩቶች ማህበር ጉባኤ ላይ ነው። በወቅቱ ከኢትዮጵያ ጋር ስዊዲን እና ብራዚል ጉባኤውን ለማስተናገድ በእጩነት ቀርበው ነበር። የኢኒስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ እንደገለጹት፤ ጉባኤው ድንበር ተሻጋሪ የህብረተሰብ ጤና ችግሮችን መከላከል በሚቻልበት መንገድ ሳይንሳዊ ምልከታንና ቴክኒካዊ ሂደቶችን ከማጠናከር ባሻገር ሙያዊ ልምድን ለማዳበርና የኢኒስቲትዩቶችን ትስስር ለመፍጠርም ያግዛል። ጉባኤው በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ጤና ዙሪያ አጀንዳዎች እየተመረጡ ውይይት የሚደረግበትና ቀጣይ የጋራ ስራዎች የሚታቀዱበት እንደሚሆንም ጠቁመዋል። በህብረተሰብ ጤና ዙሪያ ለሚከሰቱ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች እንዲሁም ከአንድ አገር ወደ ሌላ ለሚተላለፉ በሽታዎች እልባት ለመስጠት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ጉባኤው እንደሚመክርም ገልጸዋል። በአውሮፓዊያን ቀመር በ2014 እና 2015 በምዕራብ አፍሪካ አሳሳቢ የነበረውን የኢቦላ በሽታን 11 ሺ የሚሆኑ ተጠቂዎችን ለሞት መዳረጉ ብሎም ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና በአገራት ላይ ማሳደሩ ይታወሳል። ይህ በሽታ ከአንድ አመት ወዲህ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተከሰተ ሲሆን እስካሁንም በሽታውን በቁጥጥር ስር ማዋል አልተቻለም፤ በዚህም ከ2 ሺ በላይ ዜጎች መሞታቸውንም ዶክተር ኤባ ገልጸዋል። በመሆኑም አገራት እንዲህ አይነት የጤና ችግሮች ሲከሰቱ በጋራ ለመፍታት የብሄራዊ ጤና ኢኒስቲትዩቶች፣ የጤና ሚኒስትሮች እንዲሁም የዓለምና አገራዊ ተቋማትን መረጃ መሰረት በማድረግ ችግሮችን በጋራ የመከላከል ትልቅ ሚና እንዳለውም ተናግረዋል። ዘንድሮ በኢትዮጵያ የሚካሄደው ይህ ጉባኤ ከደቡብ አፍሪካ፣ ታንዛኒያና ሞሮኮ ቀጥሎ በአፍሪካ ሲካሄድ አራተኛው ነው። የአለም አቀፍ የበሽታዎች መከላከል ዳይሬክተርን ጨምሮ የአሜሪካ፣ የቻይና፣ የአውሮፓና የአፍሪካ  የበሽታዎች መከላከል ድርጅቶች ዳይሬክተሮች እንዲሁም የየአገራቱ የህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ኃላፊዎች በጉባዔው ላይ ይሳተፋሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም