በመንገዶች ላይ የተሰሩ የንግድ ሱቆች የትራፊክ አደጋ ስጋት እንደፈጠሩባቸው ነዋሪዎች ተናገሩ

61
ኢዜአ ህዳር 22/2012 ለስራ ፈጠራ ተብለው በመንገዶች ላይ የተሰሩ የንግድ ሱቆች በእንቅስቃሴያቸው ላይ ስጋት እንደፈጠረባቸው በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የቀራኒዮ አካባቢ ነዋሪዎች ተናገሩ። ነዋሪዎቹ የንግድ ቦታው በእግረኛ መንገድ ላይና በትምህርት ቤት አቅራቢያ በመቋቋሙ የትራፊክ መጨናነቅና የአደጋ ስጋት እንደፈጠረባቸው ለኢዜአ ተናግረዋል። የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 የንግድና ኢንዱስትሪ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሰይድ ፍጥረት በበኩላቸው በኢ-መደበኛ የንግድ ስራ የተሰማሩ ዜጎች በአንድ አካባቢ እንዲሰሩ በወረዳው አመራሮች በመወሰኑ ቦታው መመረጡን ገልፀዋል ። በጊዜያዊነት የተሰሩት የንግድ ሱቆች መንገድ ላይ በመሆናቸው የሚያመጡትን ችግር በመረዳት አማራጭ ቦታ ተለይቶ አሁን ካሉበት እንደሚነሱ ተናግረዋል። እንደ አቶ ሰይድ ገለጻ፤ በጊዜያዊነት የሚሰሩ ነጋዴዎች የንግድ ዘርፉ የሚጠይቀውን መስፈርት አሟልተው በወረዳው እውቅና ተሰጥቷቸው እየሰሩ ነው። የአካባቢው ነዋሪ አቶ ተሻገር በልሁ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ለወጣቱ የስራ እድል መፈጠሩ የሚደገፍ ተግባር ቢሆንም፤ የንግድ ሱቆች በእግርኛ መንገድና በትምህርት ቤት አካባቢ በመሆናቸው ህብረተሰቡን ለትራፊክ አደጋ ተጋላጭ የሚያደርጉ ናቸው። የሚመለከታቸው አካላት ይህ አይነት አሰራር የሚያመጣውን ችግር ተረድተው የተሻለ አማራጭ በመፈለግ ማስተካከያ እንዲያደርጉበት ጠይቀዋል። የአካባቢው ነዋሪ የሆኑት መምህር እንዳልካቸው ካሳ በበኩላቸው ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው በመቅረት ክፍት በሆኑ የንግድ ሱቆች ጊዜአቸውን በከንቱ እያጠፉ ስለሆነ የሚመለከተው አካል ችግሩን በመገንዘብ መፍትሄ መስጠት እንዳለበት ጠቁመዋል። በንግድ ዘርፍ የተሰማሩ አቶ ፋንታሁን ታፈረ የንግድ ቦታው ትክክለኛና ሊያሰራ የሚችል አለመሆኑን ተናግረው፤ መንግስት አመቺ የንግድ ቦታ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። አቶ ፋንታሁን አክለውም ''ቦታዉ ለትራፊክ አደጋ የተጋለጠ ስለሆነ ለጊዜውም ቢሆን የትራፊክ ፖሊስ ተመድቦ የሚደርሰውን አደጋ የመከላከል ስራ ይሰራ'' በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአዲስ አበባ እየተስፋፋ ለመጣው የመኪና አደጋ መንስኤ ከሆኑት መካከል የእግረኛ መንገዶች ለተለያዩ አገልግሎት በመዋላቸው እግረኛው የመኪና መንገድ ላይ መጠቀሙ አንድ ምክንያት እንደሆነ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም