የመንግስት ሰራተኛው የስራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን ወጥ በሆነ መንገድ ባለመተግበሩ ቅሬታ እያስነሳ ነው

84
ህዳር  22/2012 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ሰራተኛው የስራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን በተገቢው መንገድ ባለመተግበሩና ቅሬታ እያስነሳ በመሆኑ በአስቸኳይ ሊታረም እንደሚገባ አሳስቧል። የመንግስት ሰራተኛው የስራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን ፕሮጀክት በነጥብ  የሥራ ምዘና ዘዴ የተመዘኑና ደረጃ በወጣላቸው የሥራ መደቦች ላይ ተገቢውን ሠራተኛ በተገቢው ቦታ መመደብ መሆኑ ይታወቃል። ዓላማውም ሠራተኞችን በግልጸኝነት፣ በፍትሃዊነትና በተጠያቂነት አወዳድሮ በመደልደል ፐብሊክ ሰርቪሱን ውጤታማ ማድረግ ነው። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብት ልማትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንን የ2012 የመጀመሪያውን ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ዛሬ ገምግሟል። በግምገማው ወቅት እንደተጠቀሰው ምክር ቤቱ በመስክ ሄዶ እንዳረጋገጠው የመንግስት ሰራተኛው የስራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን ስራ በሁሉም ተቋማት ወጥ በሆነ መንገድ እየተተገበረ አለመሆኑን አረጋግጧል። የስራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰንን መሰረት አድርጎ ተግባራዊ ሊደረግ የነበረው የደሞዝ ማስተካከያም ተግባራዊ ባለመደረጉ በሰራተኛው ዘንድ ቅሬታን በመፍጠር የስራ ተነሳሽነትን እየጎዳው መሆኑንም አባላቱ ጠቁመዋል። መንግስት ከሐምሌ አንድ 2011 ዓ.ም ጀምሮ እንዲሻሻል የወሰነው የደሞዝ እስኬል ማስተካከያ ክፍያ ለሰራተኛው በቂ የደሞዝ ጭማሪ ይዞ ባይመጣም በተሳሳተ መልክ በሚዲያ በመነገሩ ነጋዴው በሸቀጦች ላይ ከፍተኛ ጨማሪ አድርጓል። ኮሚሽኑም ይህን አነጋጋሪ የሆነውን ጉዳይ በግልጽነትና ተጠያቂነትን ባሰፈነ ሁኔታ በተቋማት እንዲፈጽሙ አለማድረጉን አንስተዋል። በዛሬው የሶስት ወር አቅድ አፈጻጸም ግምገማ ላይም ሰራተኛውን ለቅሬታ እየዳረገ ያለውና ለሰራተኛው የስራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን ስራ መዘግየት ተጠያቂ የሆኑ አካላትን በዝርዝር አለማቅረቡም አግባብ እንደልሆነ አንስተዋል። የቋሚው ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ እምዬ ቢተው የፕሮጀክቱ አፈጻጻም ተጠያቂነትን ባሰፈነ መንገድ በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲደረግ አሳስበዋል። አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የመንግስት ተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥንና የሰው ሃብት አስተዳደርን ስርዓት ለማሻሻልም የተጀመሩ ፕሮጀክቶች መፋጠን እንዳለባቸው አሳስበዋል። የጡረተኞችን  የኑሮ ውድነት መሰረት አድርጎም ዝቅተኛ ክፍያን ለማሻሻል በቅርቡ ከተደረገው ማስተካከያ በዘለለ እየተሰራ ያለው ስራ መጠናከር እንዳለበትም በመጠቆም። ምክር ቤቱ የኮሚሽኑን ተቋማዊ አቅም ለማሳደግ እያደረገ ያለውን ጥረት፣ የተጀመሩ ጥናቶችና ፕሮጀክቶችን ለመፈጸም የሚደረገውን ጥረት ግን በበጎ ጎኑ ገምግሞታል። የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አቶ በዛብህ ገብረየስ እንዳሉት ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ለማድረግ በርካታ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ቢሰሩም በጥቂት ስራዎች ሳቢያ ወጥ በሆነ መንገድ መፈጸም አልተቻለም ብለዋል። በተለይም የተቋማት ሃላፊዎች የግንዛቤ ማነስ፣ የሰራተኛ ፍልስትና የኮሚሽኑ የማስፈጸም አቅም ውስንነት ዋነኞቹ ናቸው ብለዋል። ኮሚሽኑ በቀጣይ ይሀንን ለማስፈጸም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እንደሚሰራም ጠቁመዋል። በኮሚሽኑ ስር 250 የፌደራል ተቋማትና 20 የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እንዳሉ ጠቁመዋል። ኮሚሽኑም የተቋማት ሃላፊዎች የተሰጣቸውን የፕሮጀክት ምደባ በአግባቡ እንዲወጡ ለማድረግ በሚሰራው ስራ ምክር ቤቱ እገዛ እንዲያድርግለት ጥያቄ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም