የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ በመጪው ቅዳሜ ይጀመራል

50

ኢዜአ ህዳር 22 / 2012 የዘንድሮው የሀበሻ ሲሚንቶ የወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ የፊታችን ቅዳሜ ህዳር 27 ቀን 2012 ዓ.ም ይጀመራል። ዘንድሮ ለስምንተኛ የውድድር ዓመት በሚካሄደው የፕሪሚየር ሊጉ ውድድር ስምንት ክለቦች ይሳተፋሉ።

በዚሁ መሰረት ህዳር 27 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ከጠዋቱ 2 ሰአት ከ30 አዲስ አበባ ፖሊስ ከመከላከያ የፕሪሚየር ሊጉን የመክፈቻ ጨዋታ ያካሄዳሉ።

በተከታዩ ቀን ህዳር 28 ደግሞ ሶዶ ላይ የአምናው የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ወላይታ ድቻ ከአዲሱ የፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ ጋር ከቀኑ በ8 ሰአት ይጫወታሉ።

መዳወላቡ ዩንቨርሲቲ ከፌደራል ማረሚያ ቤቶች እንዲሁም ሙገር ሲሚንቶ በፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ሳምንት መርሃ ግብር ጨዋታቸውን ማድረግ ነበረባቸው።

ሆኖም ሙገር ሲሚንቶና ፌደራል ማረሚያ ቤቶች በቂ ዝግጅት ስላላደርግን ጨዋታው ይራዘምልን በሚል ባቀረቡት ጥያቄ ጨዋታዎቹ መራዘማቸውን የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን የውድድር ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ብሩህ ተክለማርያም ለኢዜአ ገልጸዋል።

ጨዋታዎቹ በተስተካካይ መርሃ ግብር ተይዘው ወደፊት በሚገለጽ ጊዜ እንደሚከናወኑና ጥያቄውን ያቀረቡት ክለቦች በሁለተኛ ሳምንት ጨዋታቸውን ማድረግ እንደሚጀምሩም ተናግረዋል።

በባለፈው ዓመት የፕሪሚየር ሊግ ውድድር ተሳታፊ የነበረው አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ክለብ መፍረሱን አስታውሰው ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ በሁለቱም ጾታዎች ቡድን በማቋቋም እንደሚሳተፍ ጠቁመዋል።

የዘንድሮ ዓመት የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ውጤታማ እንዲሆን የተለያዩ የዝግጅት ስራዎች ተከናውኗል ብለዋል።

በተለይም ወድድሩ ስፖርታዊ ጨዋነት በተሞላበት መልኩ እንዲካሄድ ከክለቦችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ተድርጎ የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን ነው አቶ ብሩህ ያስረዱት።

ለሁሉም ክለቦች በተጫዋቾች የዝውውር መመሪያና የውድድር ስነ ምግባር መመሪያ እንዲሁም አበረታች ቅመሞችን በተመለከተ ስልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል።

የ2012 ዓ.ም የሀበሻ ሲሚንቶ የሴቶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ እንዲካሄድ አስፈላጊው ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

እስካሁን ፌደራል ማረሚያ ቤቶች፣ ወላይታ ሶዶ ዩንቨርስቲና ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ በውድድሩ ላይ እንደሚሳተፉም ነው አቶ ብሩህ የገለጹት።

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከጌታ ዘሩ ስፖርት ክለብ ሃላፊዎች ጋር ውይይት እያደረገ መሆኑን ገልጸው ፕሪሚየር ሊጉን በታህሳስ 2012 ዓ.ም ለመጀመር እቅድ መያዙንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ በሁለቱም ጾታዎች እየተካሄደ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም