የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ማርቆስ ከተባበሩት መንግስታት ልዩ ራፖርተር ጋር ተወያዩ

85

ኢዜአ፤ ህዳር 22/2012 የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ማርቆስ ተክሌ (ዶ/ር) በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሀሳብን በነፃ የመግለፅ፣ የመጠበቅና የማስፋፋት ልዩ ራፖርተር ሚስተር ዳቪድ ካየ ከሚመራ የልዑካን ቡድን ጋር ዛሬ በጽ/ቤታቸው ተወያይተዋል።

በውይይቱ ወቅት የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ምክትል አቃቤ ህግ ዶክተር ጌድዮን ጢሞቲዎስና ባልደረቦቻቸው ተግኝተው በኢትዮጵያ ሀሳብን በነፃ የመግለፅ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ዙሪያ ለልኡካን ቡድኑ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

አምባሳደር ማርቆስ ተክሌ በበኩላቸው የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በኢትዮጵያ መጠነ-ሰፊ የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች እየተካሄዱ ነው።

በሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞና ጋዜጠኞች መፈታታቸው፣ የሚዲያ ነፃነት ያለገደብ እንዲስፋፋ መደረጉና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የተወሰዱ እርምጃዎች ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ከፍተኛ አድናቆት እንድታገኝ አስችሏታል ብለዋል።

ሚስተር ዳቪድ ካየ በበኩላቸው በበርካታ ሀገራት በተመሳሳይ አጀንዳ ዙሪያ ጉብኝት ማድረጋቸውን ጠቅሰው፥ በዛሬው እለት የተደረገላቸው ገለፃ ለየት ያለና ከፍተኛ ደስታ እንደፈጠረባቸው አንስተዋል። በኢትዮጵያ የዲሞክራሲያዊና የሰብዓዊ መብቶች ፅንሰ-ሀሳብና አተገባበር በከፍተኛ ደረጃ እያደገ በመሆኑ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ድጋፉን እንደሚቀጥል አረጋግጣለሁ ነው ያሉት።

በሚስተር ዳቪድ የሚመራው የልኡካን ቡድን በሚቀጥሉት ቀናት ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን፣ ከሰላም ሚኒስቴር፣ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ እና ሌሎች ተቋማት ጋር እንደሚወያዩ ይጠበቃል።

መረጃውን ያገኘነው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም