የቡድኑ የኡጋንዳ ቆይታ የአገራቱን የሁለትዮሽ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችል መሰረት የጣለ ነው ተባለ

65
ህዳር 22/2012 የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድኑ የኡጋንዳ ቆይታ የአገራቱን የሁለትዮሽ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችል መሰረት የጣለ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ። የኡጋንዳ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ኢትዮጵያን እንዲጎበኝም ጥሪ ተደርጎለታል። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ የተመራው የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን የአምስት ቀናት የኡጋንዳ ቆይታውን በማጠናቀቅ ትናንት ምሽት አዲስ አበባ ገብቷል። የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድኑ 50 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የስራ ሃላፊዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን ያካተተ ነው። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ ነቢያት ጌታቸው ለኢዜአ እንደገለጹት ቡድኑ በኡጋንዳ ቆይታው ንግድ፣ቱሪዝምና ባህልን ለማጠናከር የሚያስችሉ ውይይቶች በማድረግ ውጤታማ ስራ ሰርቷል። የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድኑ ጉብኝት ዓላማ የአገራቱን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር እንደበርና የተደረጉ ውይይቶችም በቀጣይ ግንኙነቱ እንዲጠናከር የሚያስችል መሰረት የጣሉ ናቸው ብለዋል። ቡድኑ በኡጋንዳ ከሚኖሩ የኢትዮጵያ ዜጎች ጋር ውይይት እንዳደረገና ከኡጋንዳ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድንም የልምድና የተሞክሮ ልውውጥ ማድረጉን ተናግረዋል። በቀጣይም የኡጋንዳ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን በኢትዮጵያ ተመሳሳይ ጉብኝት እንዲያደርግ ግብዣ  እንደተደረገለትም ጠቁመዋል። ከሁለት ሳምንት በፊትም የኢትዮጵያና ሱዳንን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ማጠናከርን ዓላማ በማድረግ የሱዳን ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን በኢትዮጵያ የሶስት ቀናት ጉብኝት ማድረጋቸውን አስታውሰዋል። የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ጉብኝቶቹ ኢትዮጵያ ከአገራቱ ጋር ያላትን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር ወሳኝ ሚና እንዳለውና በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ እየተከናወኑ ላሉ ስራዎችም ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል። የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ከኡጋንዳ ፕሬዝዳንት ዮዌሪ ካጉታ ሙሴቬኒ፣ ከአገሪቱ የፓርላማ አፈ ጉባኤ ርብቃ ካዳጋ፣ ከሀይማኖት አባቶች፣ ከማኬሬሬ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች፣ ከኡጋንዳ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት፣ ከተለያዩ ምሁራን፣ ከዓለም አቀፍ የላየን ክለብ አመራሮችና በካምፓላ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እንዲሁም ትውልድ ኢትዮጵያዊያን ጋር የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ማጠናከር በሚቻሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርጓል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም