በወላይታ ሶዶ ከተማ በንብረት ውድመትና ስርቆት የተጠረጠሩ 257 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

157
ሶዶ ሰኔ 15/2010 በወላይታ ሶዶ ከተማ ተከስቶ በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት በመንግስትና በግለሰቦች ንብረት ላይ ለደረሰው ውድመትና ስርቆት የተጠረጠሩ 257 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የወላይታ ዞን ፖሊስ መምሪያ ገለጸ። የአካባቢውን ማህበረሰብ በማሳተፍ የህዝቡን ሰላምና ጸጥታ ወደነበረበት ለመመለስ እየተሰራ ያለው ሥራ ውጤት እየተገኘበት መሆኑንም ተመልክቷል። የወላይታ ዞን ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ኤፌሶን ላካይቶ በሃዋሳና አካባቢው የፍቼ ጫምባላላ በዓል አከባበር ጋር በተያያዘ የተከሰተውን የጸጥታ ችግር ተከትሎ በወላይታ ተወላጆች ላይ ጉዳት ደርሷል። የደረሰውን ጉዳት ለመቃወም የተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ መልኩን ቀይሮ በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ አሳዛኝ ተግባር መሆኑን አስታውሰዋል። አጋጣሚውን ተጠቅሞ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ለማድረስ የተፈጸመው ተግባር የሰልፉን ዓላማ የሳተና አስተማሪነት የሌለው ተግባር በመሆኑ ተቀባይነት እንደሌላው ምክትል ኮማንደሩ ተናግረዋል። እንደምክትል ኮማንደር ኤፌሶን ገለጻ ተከስቶ በነበረው የጸጥታ ችግር የሦስት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ ከ40 በላይ ግለሰቦች ቀላልና ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ከ70 በላይ የተለያዩ ተሽከርካሪዎች በእሳት መጋየታቸውንም ምክትል ኮማንደሩ አብራርተዋል። በጸጥታ ችግር ለስርቆት ከተዳረጉ ተቋማት መካከል የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ፣ የሶዶ ግብርና፤ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋምና የኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ የሶደ ቅርንጫፍ ይጠቀሳሉ ነው ያሉት። ከዚህ በተጨማሪ የዞኑ መንገድ ልማትና ትራንስፖርት መምሪያ፣ ማዘጋጃ ቤት እንዲሁም የተለያዩ የግለሰብ ተቋማት እንደሚገኙበት ነው የገለጹት። ተቋማቱ ጉዳት ላይ እንዲወድቁና የአካባቢውን ልማት አደጋ ላይ ለመጣል ሆን ብለው የተንቀሳቀሱና በተቋማት ላይ የዝርፊያ ወንጀል የፈጸሙ 257 ግለሰቦች በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን ገልጸዋል። በህዝብ ጥቆማና ተሳትፎ የተወሰዱ ንብረቶችን የማስመለሱ ተግባር የተጀመረ ሲሆን እስካሁንም ኮምፒዩተሮችና የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲ የተወሰዱ ከ800 በላይ ፍራሾችን ማስመለስ ተችሏል። ከተለያዩ ባንኮች እንዲሁም ከብድርና ቁጠባ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የተወሰደውን ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ለማስመለስ መቻሉንም ምክትል ኮማንደር ኤፌሶን አስረድተዋል። የህዝቡንና የአካባቢውን ሰላምና ልማት የማይፈልጉ የጸረ ሰላምና ልማት ኃይሎች እንዳሉ የገለጹት ኃላፊው፣ ማህበረሰቡ ተገቢ ጥንቃቄ በማድረግ የአካባቢውን ሰላም አጠናክሮ እንዲጠበቅ ጥሪ አቅርበዋል። በቀጣይም ሕዝብን የሚያሳዝን የወንጀል ተግባር ዳግም እንዳይከሰት ሕብረተሰቡን ያሳተፈ የመከላከል ሥራ እየተከናወነ መሆኑንና ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አብራርተዋል። በህገ ወጥ መንገድ የህዝብንና የመንግስትን ንብረት የዘረፉ ወንጀለኞችን በማጋለጥ ሂደት ማህበረሰቡ የተለመደውን ትብብር ማጠናከር እንዳለበትም ጥሪ አቅርበዋል። በተለይ ወጣቱ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት ምክትል ኮማንደር ኤፌሶን ማሳሰባቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም