በቤንች ሸኮ ዞን ረዳት የሌላቸው ህፃናትን በጉዲፈቻ የማሳደግ ልምድ እየዳበረ ነው

74
ኢዜአ ህዳር 22 / 2012 በቤንች ሸኮ ዞን ረዳት የሌላቸው ችግረኛ ህጻናትን በጉዲፈቻ ተቀብሎ የማሳደግ ልምድ በህብረተሰቡ ዘንድ እየጎለበተ መምጣቱን የዞኑ ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች መምሪያ አስታወቀ። በመምሪያው የህፃናት መብትና ደህንነት ባለሙያ አቶ ይታያል እናውጋው ለኢዜአ እንዳሉት በተለያዩ ምክንያቶች ለችግር የተጋለጡ ህጻናትን በሀገር ውስጥ ጉዲፈቻ ተቀብለው የሚያሳድጉ ቤተሰቦች ቁጥር ጨምሯል። የጎዳና ተዳዳሪነት ቀደም ሲል በዞኑ ብዙም የማይታወቅ እንደነበር የጠቆሙት ባለሙያው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የጎዳና ተዳዳሪነት ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል። ይህን ችግር ለመፍታት ህብረተሰቡ ያለውን ግንዛቤ እንዲያጎለብት የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት ለጎዳና ህይወት ተዳርገው የነበሩ ህጻናትን ወደ ቤት የመመለስና ረዳት የሌላቸውን በጉዲፈቻ ለሚያሳድጉ ቤተሰቦች የመስጠት ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል። በህብረተሰቡ በተፈጠረ ግንዛቤም ረዳት የሌላቸው 16 ህጻናት በጉዲፈቻ ለሚያሳድጉ ቤተሰቦች መሰጠቱን ገልፀዋል፡፡ ሌሎች 64 ህጻናት ደግሞ  በህብረተሰቡ ድጋፍ እንዲያገኙ እየተደረገ ሲሆን 63 ህፃናት ደግሞ ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ መደረጉን ገልጸዋል። ህፃናትን በጉዲፈቻ ተቀብለው ከሚያሳድጉት መካከል በሚዛን አማን ከተማ የሻሸቃ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ችጌ ጋሞና ባለቤታቸው አቶ ይሉ ባይሳ አንድ ህፃን ወስደው እያሳደጉ መሆኑን ተናግረዋል። ህጻኑን እንደ ልጃቸው ለማሳደግ በህጋዊ መንገድ ተረክበው ተገቢውን እንክብካቤ በማድረግ እያስተማሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል። ''ከወለድናቸው ልጆች እኩል ያለምንም ልዩነት እያሳደግን እንገኛለን፤ የሚያስፈልገውን ሁሉ በማሟላት ለወግ ማዕረግ እናበቃለንም'' ብለዋል። ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ ዘሀራ መሀመድ በበኩላቸው ህጻኑን ወስደው ማሳደግ መቻላቸው የህሊና እርካታ እንደሰጣቸው ጠቁመዋል። ልጅ ማሳደግ ከባድ ቢሆንም አሳዳጊ አጥቶ ለጎዳና የተዳረገ ህፃንን ማሳደግ ሰብዓዊነት መሆኑን ወይዘሮ ዘሀራ ተናግረዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም