ፖለቲከኞች እጃቸውን ከትምህርት ቤቶች እንዲያነሱ ተጠየቀ

90
ኢዜአ ህዳር 21/2012 ዓ/ም መንግስት ትምህርት ቤቶችን ለፖለቲካ አጀንዳቸው ማስፈጸሚያ የሚጠቀሙ አካላት ላይ ጠበቅ ያለ እርምጃ ሊወስድ ይገባል ሲሉ በደቡብ ክልል የመምህራን ማህበር አመራሮች ገለፁ ። በየትምህርት እርከኑ ለደረጃው ብቁ የሆኑ መምህራን በመመደብ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በልዩ ትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም ጠቁመዋል። አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የመምህራን ማህበራት አመራሮች እንዳሉት በአሁኑ ሰዓት ትምህርት ቤቶች ከመማር ማስተማር ስራ ይልቅ ለፖለቲካ አመለካከት ማንጸባረቂያ መድረክነት ለማዋል የሚደረጉ ጥረቶች በመኖራቸው መንግስት  ተከታትሎ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል ። የዳውሮ ዞን መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት መምህር አስረስ አበራ እንደገለፁት የተለያዩ የፖለቲካ አጀንዳ ያላቸው አካላት ትምህርት ቤቶችን መጠቀሚያ ለማድረግ የሚንቀሳቀሱበት አጋጣሚ መኖሩን ተናግረዋል ። በክልሉ አንዳንድ አከባቢዎች ከጸጥታ ችግር ጋር ተያይዞ ዛሬም ድረስ የትምህርት ስራ ያልተጀመረባቸውና የመምህራን ደመወዝ ጭምር ያልተከፈለበት ሁኔታ መኖሩን ጠቁመው በማሳያነት ሰገን ዙሪያ ወረዳን አንስተዋል። በዚህ አካባቢ ያለውን የጸጥታ ችግር በመጠቀም የግል የስልጣን ጥታቸውን ለማርካት የሚራወጡ አካላት እንዳሉ ጠቁመዋል። በዚህም ምክንያት ተማሪዎች በአግባቡ ትምህርታቸውን መከታተል ያልቻሉበትና መምህራንም ደሞወዝ ሳይከፈላቸው የሚቆዩበት ሁኔታ መኖሩን ገልፀው የክልሉ መንግስት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት መስራት አለበት ብለዋል። የጉራጌ ዞን መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት መምህር በርታ ያረብ በበኩላቸው በክልሉ የመማር ማስተማር ሂደቱ በተለያዩ አጋጣሚዎች መቆራረጡ በትምህርት ጥራቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ መሆኑን ተናግረዋል ። በክልሉ የመምህራን ጥቅማ ጥቅም ከማስከበር ረገድ ክፍተቶች ቢኖሩም መምህራን ለችግሮች ሳይሸነፉ ትክክለኛውን የትምህርት ስርዓት በትክክለኛው ጊዜ ለተማሪ ለማድረስ የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል ። ከመምህራን ውጭ ለትምህርት ጥራት ወሳኝ ሚና ያላቸው ባለድርሻ አካላትም በየትምህርት እርከኑ ለደረጃው ብቁ የሆነ መምህር በመመደብ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በልዩ ትኩረት መስራት አለባቸው ብለዋል። የደቡብ ክልል መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ አማኑኤል ጳውሎስ እንዳሉት ደግሞ በተጠናቀቀው የትምህርት ዘመን በክልሉ 10 በሚደርሱ ዞኖች በርካታ ትምህርት ቤቶች በጸጥታ ችግር ምክንያት የመማር ማስተማር ሂደትቱን ለማቋረጥ ተገድደው ነበር ። በተደረገው ጥረት በርካታ ትምህርት ቤቶች ወደ ስራ የገቡ ቢሆንም በሰገን ዙሪያ ወረዳ ግን ዛሬም ድረስ 7 ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ስራቸው አልጀመሩም ብለዋል ። ከጸጥታ ችግር ውጭ የመምህራን ደሞዝን ጨምሮ ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች በወቅቱ አለመከፈሉን ተከትሎ መምህራን የትምህርት ስራን ዘግተው ለአቤቱታ የሚሄዱበት አጋጣሚ መኖሩን ገልጸዋል። በዚህም የትምህርት ብክነት እያጋጠመ በመሆኑ የትምህርት ስራውን ውጤታማ ከማድረግ አንጻር የትምህርት አመራሩ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል። የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ ማትዮስ ማልዳዬ በበኩላቸው በጸጥታ ችግርም ሆነ በመምህራን ጥቅማ ጥቅም አለመከበር ሳቢያ የትምህርት ብክነት መፈጠሩ በትምህርት ጥራት ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩን ገልጸዋል። በየደረጃው ካሉ ባለደርሻ አላላት ጋር ውይይት በማድረግ በተያዘው የትምህርት ዘመን ችግሩን ፈር በማስያዝ ሁሉንም ትምህርት ቤቶች በተረጋጋ መልኩ የመማር ማስተማር ስራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም