መቀሌ ሰባ እንደርታ እና ወላይታ ድቻ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸነፉ

78
ኢዜአ ህዳር 21/2012 በኢትዮጰያ ፕሪሜየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት ዛሬ በመቀሌ በተካሄደው የእግር ኳስ ጨዋታ መቀሌ ሰባ እንደርታ ሐዲያ ሆሳእናን ሁለት ለአንድ አሸነፈ። ወላይታ ድቻ ደግሞ በሜዳው ሲዳማ ቡናን አስተናግዶ ሁለት ለባዶ ረቷል። በመቀሌ ብዝግ ስታዲዮም በተካሄደው ጨዋታ በ53ኛው ደቂቃ መቀሌ ሰባ እንደርታ በአስር ቁጥሩ በያሬድ ከበደ አማካኝነት የመጀመሪያውን ግብ ከአንድ ደቂቃ በኋላ ደግሞ በ11 ቁጥሩ አማኑኤል ገብረሚካኤል አማካኝነት ሁለተኛው ማስቆጠር ችሏል። በሃዲያ ሆሳእና በኩል 60ኛው በደቂቃ ላይ በሁለት ቁጥሩ ደስታ ግቻሞ አንድ ግብ አስቆጥሮ በዚሁ ውጤት ተበልጦ በመቀሌ ሳባ እንደርታ አሸናፊነት ጨዋታው ተጠናቋል። የመቀሌ ሳባ እንደርታ አስልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ በሰጡት አስተያየት “ማሸነፋችን ጥሩ ቢሆንም ብዙ እንቅስቃሴ ያላሳየንበት ምክንያት ያለተመልካች በዝግ ስታዲዮም በመጫወታችን ጥሩ እንቅስቃሴ አላሳየንም” ብለዋል ። በቀጣይ ውድድር በቅጣትና በጤና ምክንያት የተጓደሉ ተጫዋች አሟልተው ጥሩ ውጤት ለማምጣት እንደሚዘጋጁ ተናግረዋል። የሃዲያ ሆሳእና አሰልጣኝ ኢዘዲን አብደላ በበኩላቸው “በዝግ ስታዲየም በመጫወታችን ፉክክራችን ቀዝቃዛ ቢሆንም ቆንጆ ተጫውተናል፤ ያገኘነው ውጤት ሽንፈት ቢሆንም በቀጣይ ጉድሎቶቻችንን አስተካክለን ጥሩ ተፎካካሪ እንሆናለን “ ሲሉ ገልጸዋል። በተመሳሳይ ዛሬ በተጀመረው የዘንድሮ የኢትዮጵያ የወንዶች ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ የደቡብ ደርቢ  ወላይታ ድቻና ሲዳማ ቡና  ተገናኝተዋል። ባለሜዳው የወላይታ ድቻ ግቦችን ያስቆጠረው በ48ኛው ደቂቃ አስር ቁጥሩ ባዬ ገዛኸኝና በስምንት ቁጥሩ እድሪስ ሰይድ በ79ኛው ደቂቃዎች ላይ ነው። በሁለቱም ቡድኖች መካከል የነበረው እንቅስቃሴ እምብዛም ለተመልካች ሳቢ ባልነበረው የመጀመሪያው ዙር ጨዋታ ያለምንም ግብ ነው ሆኖም በአንጻራዊነት ኳስ በማደራጀትና ወደተጋጣሚው የግብ ክልል በመድረስ ረገድ ድቻ የተሻለ ነበር። ሁለተኛው ዙር ጨዋታ መጠነኛ የተጨዋች ለውጥ በማድረግ በሁለቱም ቡድኖች መካከል በፈጣን የመሃል ሜዳ የኳስ ፍሰትና ሙከራዎች ታጅቦ ነው የተጀመረው። የሲዳማ ቡና ቡድን ኳስ በማደራጀትና የመሃል ሜዳውን ብልጫ ለመውሰድ ያደረጉት ጥረት አልተሳካላቸውም እንጂ መልካም ነበር። በዚህ ሂደት ጨዋታው ቀጥሎ ወላይታ ድቻ ባስቆጠራቸው ሁለት ግቦች አሸንፎ ሊወጣ ችሏል። የሁለቱም ቡድኖች ደጋፊዎች በተሟላ ስፖርታዊ ጨዋነት ቡድኖቻቸውን አበረታትተዋል። በእግር ኳስ ሜዳ በሚፈጠሩ ስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለት ምክንያት በሜዳቸው እርስ በርስ መስተናገድ ካቆሙ አንድ ዓመት በላይ የሆናቸው ሁለቱም ቡድኖች ደጋፊዎቻቸው ያለምንም የጸጥታም መጠናቀቁ ከምንም በላይ እንዳስደሰታቸው የድቻ ዋና አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ተናግረዋል። “ከምንም በላይ ለሰው ልጅ ሠላም ያስፈልጋል “ያሉት አሰልጣኙ ባላደገው የሀገሪቱ እግር ኳስ ሠላምን ማጣት ተገቢ ባለመሆኑ ደጋፊው ሰላምን ሊያስቀጥል እንደሚገባም ጠቁመዋል። የሲዳማ ቡና አቻቸው ዘራይ ሙሉ በበኩላቸው “የከተማው ነዋሪ ያሳየው አቀባበልና በደጋፊዎች መካከል የተፈጠረው ሠላማዊ ግንኙነት መልካምነት ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል ጨዋታውን በፈለጉት መልክ ተቆጣጥረው ለመጫወት ሜዳው እንዳልፈቀዳቸው ገልጸው ተጋጣሚው ያገኘውን ዕድል በአግባቡ በመጠቀሙ ሊያሸንፋቸው እንደቻለ ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም