በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፈን ምዕምናን በጸሎትና ምህላ መጠንከር አለባቸው ---ብጹእ ወቅዱስ አቡነማቲያስ

153
ኢዜአ ኀዳር 21/2012 በመላ ኢትዮጵያ ሰላም ሰፍኖ መረጋጋት እንዲመጣ ሁለም ምዕመናን በጸሎትና ምህላ መጠንከር እንዳለባቸው  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አሳሰቡ። የአክሱም ጽዮን ዓመታዊ የንግስ ክብረ በዓል ዛሬ በደምቀት ተከብሯል። በበዓሉ ስነስርዓት ወቅት  ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ “ሰላም ለሁሉም ፍጡር ወሳኝ እና ልንጠብቀው የሚገባ ዋጋ የማይገኝለት ጸጋ ነው “ ብለዋል። በመላ ኢትዮጵያ ሰላም ሰፍኖ መረጋጋት እንዲመጣ ሁሉም ምዕመናን በጸሎትና ምህላ መጠንከር እንዳለባቸው አሳስበዋል። “የእኛን ክፍተት እና መዳከም እያዩ የኢትዮጵያን ጉዳት የሚመኙ ብዙ ናቸው፣ክፍተት አስወግደን አንድነታችን ልናጠናክር ይገባል “ብለዋል። የኢትዮጵያ ህብረት፣አንድነት እና ጽናት ተጠብቆ እንዲኖር እያንዳንዱ ዜጋ በትጋት መስራት እንዳለበት ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። በበዓሉ ስነስርዓት የተገኙት የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በበኩላቸው ትግራይ የብዙ ኃይማኖታዊ ፣ባህላዊ ፣ታሪካዊ ቅርስ ሃብት ባለቤት መሆኗን ተናግረዋል። ይህንን ሀብተ ለአለም ማህበረሰብ በማስተዋወቅ ለቱሪዝም ልማት ማዋል እንደሚገባ ጠቁመዋል። “በዓሉ ስናከብር አንድነታችን እና ሰላማችን ጠብቀን ፌዴራላዊ እና ህገ መንግስታዊ ስርዓት እንዳይፈርስ በጋራ መስራት ያስፈልጋል” ብለዋል። በበዓሉ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎችና ከውጭ የመጡ የእምነቱ ተከታዮችና እንግዶች በተገኙበት በደመቀ ስነስርዓት ተከብሯል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም