የመልካ ሶር ኢሬቻ በዓል በድምቀት ተከበረ

88
መቱ ህዳር 21/2012 የመልካ ሶር ኢሬቻ በዓል በኢሉአባቦር ዞን መቱ ከተማ ከምዕራብ ኦሮሚያ አጎራባች ዞኖች የመጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት ዛሬ በድምቀት ተከበረ። በዓሉን ምክንያት በማድረግ ትናንት በመቱ ከተማ   የፓናል ውይይትና ሌሎችም ስነስርዓቶች ተካሄደዋል። ዛሬ በተከበረው በዓል የሰግለን ኢሉአባገዳ ከሊፋ ሾኖ እንዳመለከቱት ህብረተሰቡ እና የመንግስት አካላት የኦሮሞ ህዝብ ጥንታዊ ባህል እንዲጎለብት እያደረጉ ያለው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። የመጀመርያው የሰግለን ኢሉ አባገዳ ለነበሩት ጫሊ ሾኖ (አባቦራ)የመታሰቢያ ሐውልት ለማቆም የመሰረተ መቀመጡ መደሰታቸውን ገልጸው ህብረተሰቡ በነቂስ በመውጣት በዓሉን በማክበሩ ምስጋና አቅርበዋል። የጅማ ዩኒቨርስቲ መምህር ዶክተር ደረጀ ፉፋ የኦሮሞ ህዝብ ኢሬቻን ጨምሮ ሌሎች ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶችን ለማጎልበት በትኩረት እንዲሰራ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። የጥንታዊው የሰግለን ኢሉ የገዳ ስርዓት አካል የሆነው የመልካ ሶር ኢሬቻ በምዕራብ ኦሮሚያ ትልቁ የኢሬቻ በዓል እንደሆነ የገለጹት ደግሞ  የኢሉአባቦር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ግርማ ረጋሳ ናቸው። ይህንን የኢሬቻ በዓልና ሌሎች ጥንታዊ የኦሮሞ ህዝብ ባህላዊ እሴቶች ለመንከባከብና ለማሳደግ የዞኑ አስተዳደር የበኩሉን እንደሚወጣ አስታውቀዋል። የአካባቢው ህዝብ ባህል እና ታሪክ በስነፅሑፍ በማስተዋወቅ ረገድ ውስንነት እንዳለ ጠቅሰው በዚሁ መስክ ምሑራንና የስነፅሑፍ ባለሙያዎች የበለጠ ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክተዋል። የመልካ ሶር ኢሬቻ በዓል የጥንታዊው የሰግለን ኢሉ ገዳ ስርዓት አካል ሲሆን በኢሉአባቦር ዞን መቱ ከተማና አካባቢው የሚከበር ነው። በበዓሉ ስነስርዓት ከምዕራብና ምስራቅ ወለጋ፣  ከኢሉአባቦር እና ቡኖ በደሌ ዞኖች የመጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል። የመልካ ሶር ኢሬቻ በዓል ምክንያት በማድረግ ትናንት በመቱ ከተማ   የፓናል ውይይት የተካሄደ ሲሆን የዞኑ ባህላዊ ምግቦች ቀርበዋል፤ እንዲሁም የመጀመርያው የሰግለን ኢሉ አባገዳ ለነበሩት ጫሊ ሾኖ(አባቦራ) የመታሰቢያ ሀውልት ለማቆም የመሰረተ ድንጋይ ተቀምጧል:: የመታሰቢያ ሐውልቱ ግንባታ የሚከናወነው በሰግለን ኢሉ ገዳ ስርዓት መቀመጫ ያዮ ከተማ ነው።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም