ከመንገድ ትራፊክ አደጋ የተጠበቀ ቀን እንዲኖር ምን ማድረግ እንደሚጠበቅበት ሁሉም ራሱን ይጠይቅ - ትራንስፖርት ሚኒስቴር

56
ኢዜአ ህዳር 20/2012 ዓም ሁሉም ሰው ከመንገድ ትራፊክ አደጋ “እኛስ ከመንገድ ትራፊክ አደጋ የተጠበቀ ቀን እንዲኖረን ምን ማድረግ ይጠበቅብናል?” ብሎ ራሱን እንዲጠይቅና ድርሻውን እንዲወጣ የትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ አሳሰቡ። በዓለም 14ኛውና በሃገራችን 12ኛው የዓለም የመንገድ ትራፊክ አደጋ ተጎጂዎች መታሰቢያ ቀን “ህይወት የተሽከርካሪ አካል አይደለም መለዋወጫ የለውም!” በሚል ዛሬ በአዲስ አበባ ተከብሯል። ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የሀገራችን አሳሳቢ አደጋ የሆነው የትራፊክ አደጋን ለመከላከልና ለመቀነስ የትራንስፖርት ዘርፍ ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ትብብርና ርብርብ የሚጠይቅ ነው ብለዋል። ስለሆነም ዕለቱ ጉዳቱንና ተጎጂዎችን አንድ ቀን አስበን የምንውልበት ሳይሆን ህብረተሰባችን ስለአደጋው  የተሻለ ግንዛቤ የሚጨብጥበትና የድርሻውን ለመወጣት ቃል የሚገባበት እንዲሆን ተመኝተዋል። የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማትም በአግባቡ የማሰልጠን፣ የምርመራ ተቋማትም በአግባቡ የመመርመር፣ የጥገና ተቋማትም እንዲሁ ኃላፊነታቸውን በተገቢው መንገድ መወጣት አለባቸውም ብለዋል። እንዲሁም የተሽከርካሪ ባለንብረቶች፣ ህግ አውጪዎች፣ ተቆጣጣሪ አካላት፣ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ መላው ህብረተሰብ በተናጠል የሠራቸውን በመጭመቅ ለተሻለ ውጤት ሲሠራ አደጋውን መቀነስ ያስችላልም ብለዋል ሚኒስትሯ። ሚኒስትሯ አክለውም " እኔ አለአግባብ በምሰራው ስራ የምጎዳው ራሴን፣ መላ ቤተሰቤን፣ ወገኔንና መላው ማህበረሰቤን ነው" ብሎ ማሰብ ከሁላችንም ይጠበቃል ብለዋል። አደጋውን ለመቀነስም ሚኒስቴሩ የመንገድ ደህንነት ትምህርት በመደበኛ ስርዓት እንዲካተትና ከዓለም ባንክ በተገኘው ድጋፍ አጠቃላይ የመንጃ ፈቃድ አሰራር፣ የተሽከርካሪ ፍተሻና ቁጥጥር ስርዓቱን ለማዘመን እየሰራ ነው። የመንገድ ደህንነት ስራን በጠንካራ አደረጃጀት የሚመራ ተቋምም ልዩ ትኩረት አግኝቶ እየሠራ መሆኑንና አደጋ ይደርስባቸዋል ተብለው በተለዩ ከ2 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ መንገዶች ላይ የምህንድስና ማሻሻያ እያደረገ መሆኑ ተገልጿል። እንዲሁም ሚኒስቴሩ የተሻለ የፍጥነት ወሰን ገደብንና የደህንነት ቀበቶውን በተሰፋሪዎችም ተግባራዊ ለማድረግ በቅርቡ የተጀመረው ስራ ይገኝበታል ብለዋል። በዓሉን ምክንያት በማድረግ የተጀመረው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራም ከዛሬ ጀምሮ በመላ አገሪቷ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ እስከታች ባሉ አደረጃጀቶች እስከ ታህሳስ 30 የሚቀጥል ይሆናልም ብለዋል። በ2011 ዓ.ም ብቻ አደጋውን መካላከልና መቆጣጠር በሚቻለው የመንገድ ትራፊክ አደጋ 4 ሺህ 597 የሞት፣ 7ሺህ 407 የከባድ አካል ጉዳትና 5ሺህ 949 ቀላል የአካል ጉዳት ምክንያት ከመሆን ባሻገር አገራችን የ870 ሚሊዮን ብር ንብረት ውድምት  አጋጥሟታል ብለዋል። የዓለማችን የትራፊክ አደጋዎች እውነታ በየ24 ሴኮንድ በመንገድ ትራፊክ አደጋ 1 ሰው ህይወቱን እንደሚያጣ ይገልጻል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም