ኢትዮጵያ ሳተላይቱን ካመጠቀች ለኪራይ ከምታወጣው ገንዘብ በአመት ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ ያስቀርላታል

133
ኢዜአ ህዳር 21/2012 ኢትዮጵያ የራሷን ሳተላይት ካመጠቀች በዓመት ለኪራይ ታወጣው ከነበረው ገንዘብ ውስጥ ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪን ማስቀረት እንደሚችል የኢትይጵያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ገለጸ። ኢትዮጵያ የራሷን ሳተላይት ለማምጠቅ ቀነ ቀጠሮ ይዛለች። በቻይና የተሰራችውና 72 ኪሎ ግራም የምትመዝነው ሳተላይት ታህሳስ 10 ቀን 2012 ዓ.ም ከቻይና ቤጂንግ 400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትወነጨፋለች ተብሎም ይጠበቃል። ይህች ከመሬት በ700 ኪሎ ሜትር ርቃ ርቃ እንደምትቀመጥ የተገለጸችው ሳተላይት ታዲያ አገሪቷን በአካባቢ ጥበቃ፣ በግብርና እና በአየር ሁኔታ መረጃ በመስጠት እንደምታገለግል ተነግሯል። የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን በላይ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት ኢትዮጵያ የራሷን የሳተላይት ቴክኖሎጂ መጠቀሟ ከቀሪው ዓለም ጋር ተወዳዳሪ ሆና እድገቷን ለማፋጠን ይረዳታል ብለዋል። እስካሁን በነበረው ሁኔታ ኢትዮጵያ የተለያዩ መረጃዎችን ለመሰብሰብ ቴክኖሎጂው ላላቸው አገራት በርካታ የኪራይ ገንዘብ ትከፍል እንደነበርና ይህ ሳተላይት ጥቅም ላይ ሲውል ግን በዓመት ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪን ማስቀረት እንደሚቻላት ነው የተናገሩት። በሳተላይቱ በአጠቃላይ በአገሪቷ ውስጥ ያሉ አስፈላጊ መረጃዎችን በአራት ቀናት ውስጥ አደራጅቶ ማምጣት እነደሚቻልም ነው የገለጹት። ግብርናን ጨምሮ በሌሎች የአገሪቷ የኢኮኖሚ ዘርፎች ዙሪያ አስፈላጊ መረጃዎችን በሚፈለገው ፍጥነትና ጥራት ለማግኘትም ትልቅ ሚና እንደሚኖረውም እንዲሁ። የሳተላይት ቴክኖሎጂው ከቻይና መንግስት ጋር በተደረገ ትብብር የተገነባ ሲሆን ይህም ለአገሪቷ አስተማማኝ መረጃን በማቅረብና በመረጃው ላይ በቂ ትንታኔ በማድረግ ፖሊሲ አውጪዎችም ጭምር እንዲጠቀሙበት ለማድረግ ያግዛል ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪም በዘርፉ ብቁ የሰው ኃይል እንዲኖር ጥሩ ተሞክሮ እሚወሰድበትና ቀጣይም የሳተላይት ቴክኖሎጂውን በአገሪቷ ውስጥ በማሳደግ ለአጎራባች አገራት እስከ ማከራየት ለመድረስ ያለመ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። ይሁን እንጂ አንድ ሳተላይት ለአንድ አገር በቂ አለመሆኑንና በቀጣይም ይህንኑ ጅምር አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም ገልፀዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም