በአባያና ጫሞ ሀይቅ የአሳ ሀብት እየተመናመነ ነው

138
ኢዜአ ህዳር 21/2012  በአባያና ጫሞ ሀይቅ የሚገኘው የአሳ ሀብት በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ጫና ምክንያት እየተመናመነ መምጣቱ ተገለጸ። ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኝ የጋሞ ዞን እንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት መምሪያ ገልጿል። ኢዜአ ያነጋገራቸው አሳ አስጋሪዎች እንደተናገሩት በህገወጥ አሳ አስጋሪዎችና በሀይቁ ዙሪያ የሚገኝ መሬት ለእርሻ ስራ መዋሉና በፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻ በሀይቁ ላይ የሚደርሰው ብክለት የአሳ ሀብቱ ላይ መመናመን አስከትሏል። የጫሞ አስጋሪዎች ህብረት ስራ ማህበር ሰብሳቢ አቶ ቶማስ ከርባ እንዳሉት በዓባያና ጫሞ ሀይቆች ህገ-ወጥ አስጋሪዎች ከኬሚካል ንክኪ ያለው መረብ በመጠቀም የሚደረግ አሳ የማስገር ስራ ጉዳት እያደረሰ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ከዚህ ቀደም በብዛት ይገኝ የነበረው ዓሳ አሁን ላይ እየተመናመነ መምጣቱ ህጋዊና በማህበር ተደራጅተው ግብር እየከፈሉ የሚሰሩ አስጋሪዎች ኑሮ ላይ ጫና እንዳሳረፈ ገልጸዋል። የሚመለከተው አካል ይህን ችግር ተከታትሎ መፍትሄ ሊፈልግለት እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡ የነጭ ዓባይ አሳ አስጋሪዎች ማህበር ሊቀመንበር አቶ ተስፋዬ ዳታ በበኩላቸው እንዳሉት በሀይቁ ዳርቻ የሚገኘው መሬት ለእርሻ ስራ መዋሉ አፈሩ በውሀ እየታጠበ ወደ ሀይቁ በመግባት በደለል እንዲሞላ እያደረገው ይገኛል። በሀይቁ ዳርቻ የሚገኘውን መሬት በህገወጥ መንገድ ለእርሻ ስራ የሚያውሉ ግለሰቦች መበራከታቸውን ጠቁመው ይህን ማስቆምና በአካባቢው የተፋሰስ ልማት ስራን በትኩረት መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል። የጋሞ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ የእንስሳት ጥራት ባለሙያ የሆኑት ወይዘሮ ኢትዮጵያ ዘነበ እንዳሉት በሀይቆቹ ዙሪያ የሚገኙ ከተሞች ደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ ወደ ሀይቁ እየገባ በመሆኑ ለዓሳ ምርት መቀነስ የራሱ አስተዋጽኦ አለው። ከዚህም ባለፈ ጫጩት አሳዎች በህገወጥ አስጋሪዎች ለገበያ እየቀረቡ መሆኑ ለዓሳ ሀብቱ መመናመንና በምርት ጥራት ላይም ተጽእኖ ማሳረፉን ገልጸዋል። ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ቢሆንም በአመራር መፈራረቅ ምክንያት ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንዳልቻለ ጠቁመዋል። የጋሞ ዞን እንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት መምሪያ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ሲመኙሽ አጭዳ እንዳሉት የአባያና ጫሞ ሀይቆች በአመት ከ5ሺህ ቶን በላይ ዓሣ የማምረት አቅም ቢኖራቸዉም በአሁኑ ሰዓት ከ3ሺህ ቶን በላይ ምርት ማግኘት አልተቻለም። ሀይቆቹ በደለል መሞላት፣ የሃይቁ ብክለት፣ በሀይቁ ዳርቻ ያለው መሬት ያለመከበር፣ መጤ አረምና ህገ-ወጥ አስጋሪዎች ለዓሣ ዝሪያዎችና ምርት መቀነስ ምክንያት ናቸው ብለዋል። ከተፈጥሮ ሀብት መመናመን ጋር በተያያዘ የሚከሰተውን ችግር ለመፍታት የተፋሰስ ልማት ስራ ላይ በማተኮር የችግኝ ተከላ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ለዓሣ አስጋሪዎች ማህበራትም የሚገለገሉባቸው የማስገሪያ መሣሪያዎች አጠቃቀም ዙሪያ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ይሁን እንጂ የተሠሩ ሥራዎች በቂ ባለመሆናቸው የሀይቆችን ህልውና ሙሉ በሙሉ መታደግ እንዳልተቻለ ጠቁመዋል፡፡ በያዝነዉ የበጀት ዓመት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከዘርፉ ግብረ-ኃይልና ጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በህገ-ወጦች ላይ ህጋዊ እርምጃ የመውሰድ ስራ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም