በሀውዜን የተሰዉት ኢትዮጵያውያን የማንነታችንና የነጻነታችን መሰረቶች ናቸው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ

78
አዲስ አበባ ሰኔ 14/2010 ለአገራዊ አንድነት ትናንት መሰረት መሆኑ ሲገለጽ "በሀውዜን የተሰዉት ኢትዮጵያውያን የማንነታችንና የነጻነታችን መሰረቶች ናቸው ማለት ነው"  ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር  አብይ አህመድ ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ሰኔ 15 ቀን 1980 ዓ ም ከረፋዱ 5 ሰዓት ገደማ በሀውዜን ለተፈጸመው ጭፍጨፋ መታሰቢያ መልዕክት አስተላልፈዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በንጹሃን ዜጎች ላይ “በደረሰው ዘግናኝ ጭፍጨፋ” የሚሰማቸውን “ጥልቅ ሀዘንና የልብ ስብራትም” በመልዕክታቸው አካተዋል፡፡ በተፈጸመው የአየር ጥቃት 2 ሺ 500 ንጹሃን ከተቀጠፉ ዓመታት ማለፉን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤  ህመሙና ሃዘኑ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ስለማይሽር ለሁልጊዜውም እየዘከረው ዛሬ ላይ መድረሱን ገልጸዋል። ለዛሬው አገራዊ አንድነትና ኢትዮጵያዊነት ህልውና ትናንት መሰረት መሆኑን አጽንኦት የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በሀውዜን የተሰውት ኢትዮጵያውያን የማንነትና የነጻነት መሰረት መሆናቸውንም  ነው የገለጹት። ''በሀውዜን ምድር የጨካኞች መዳፍ ህይወታቸውን የነጠቃቸውን ወገኖቻችንን ይበልጥ ከማክበር፣ ከመዘከርና ታሪካቸውን ከመከተብ ረገድ ሁሉም ዜጋ በተገቢው መንገድ የቤት ስራውን እንዲሰራ"   ጥሪ ያቀረብት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መንግስትም የሰማዕታቱን ክብር በተገቢው ከፍ ለማድረግ አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል። መንግስት ካለፈው ታሪክ ተምሮ ትናንት የገጠመን ዓይነት መዓት እንዳይገጥም አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ቃል ኪዳኑን እንዳሚያድስ አመልክተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት መንግስት ያሰበው የሚሳካው ህዝቡ ከጎኑ ቆሞ ጥሩውን ሲደግፍ እና ልክ ያልሆነውንም በምክንያት ሲነቅፍ እንደሆነም አስገንዝበዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሙሉ መልዕክት ከዚህ ያገኛሉ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም