ከህግና መመሪያ ውጭ በሚሰሩ የትምህርት ተቋማት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል

141

ኢዜአ ህዳር 20 ቀን 2012 ከህግና መመሪያ ውጭ በሚሰሩ የትምህርት ተቋማት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ የግል ከፍተኛ ትምህርትና የቴክኒክ ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ማህበር ጠቅላላ ጉባዔ ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በጉባዔው መክፈቻ ላይ የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ታምራት ሞታ እንደተናገሩት፤ በትምህርት ዘርፉ ላይ በኃላፊነት የሚሰሩ በርካታ ተቋማት ቢኖሩም ከህግና መመሪያ ውጭ ትርፍን ብቻ ማዕከል በማድረግ የሚሰሩ ተቋማትም አሉ።

ይህም በዘርፉ ላይ የሚስተዋል አሳሳቢ ችግር ከመሆኑም ባሻገር ብቁ ዜጋን ከማፍራት አኳያ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድር በመሆኑ ኤጀንሲው ተገቢውን እርምጃ የመውሰድ ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

እንደ አቶ ታምራት ገለጻ ፤ በትምህርት መመሪያው ከተቀመጡ መስፈርቶች ውጭ ተማሪዎችን የመቀበል፣ ያለ እውቅና ፈቃድና ዕድሳት የትምህርት ፕሮግራሞችን የመክፈት ችግሮች ይታያሉ።

የግብዓት እጥረቶች፣ ብቃት ያለው የሰው ሃይል አለማሟላትና ሌሎች ችግሮች እንደሚስተዋሉም ገልጸዋል።

ከህግና መመሪያ ውጭ የሚሰሩ ተቋማትን ለመቆጣጠርና ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የህብረተሰቡና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ርብርብ የሚጠይቅ እንደሆነም አመልክተዋል።

በግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን ለመከታተል የሚፈልጉ ተማሪዎችና ወላጆቻቸው ከእውቅና እና ዕድሳት ጋር በተያያዘ የተሟላ መረጃ ሊኖራቸው እንደሚገባም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ የግል ከፍተኛ ትምህርትና የቴክኒክ ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ሞላ ፀጋዬ በበኩላቸው ማህበሩ በዘርፉ የተሰማሩ ተቋማት ህግና ስርዓትን አክብረው እንዲሰሩ እንዲሁም የህግ ጥሰትን ለመከላከል ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የማህበሩ አባላት ቁጥር 110 ሲሆን በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ላይ ቁጥሩን 140 ለማድረስ መታቀዱን ዶክተር ሞላ ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ በአራት ክልሎች የማህበሩን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ለመክፈት ጥረት እንደሚደረግም ገልጸዋል።

በትምህርት ላይ ከሚሰሩ አገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በጋራ ለመስራት ማህበሩ ዕቅድ መያዙን ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ 238 የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንደሚገኙ ከከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም