በተደጋጋሚ እየፈረሱ የሚገነቡ የመንገድ አካፋይ ጉብታዎች ጉዳይ ተመልካች ይሻል

42

ኢዜአ ህዳር 20 ቀን 2012 መንገዶች ከሚሰጡት አገልግሎት በተጨማሪ ከተማን የማስዋብ ተግባር ይገኝበታል፤ የመንገድ አካፋይ ጉብታዎች ለዚህ ተጠቃሽ ናቸው።

ሆኖም በአዲስ አበባ አንዳንድ አካባቢዎች እነዚህ የመንገድ አካፋይ ጉብታዎች ይገነባሉ ምክንያቱ ሳይታወቅም እንዲፈርሱ ይደረግና በድጋሚ በተመሳሳይ ቁስ ይገነባሉ።

ይህ ሁኔታ በተደጋጋሚ ከሚስተዋልባቸው አካባቢዎች መካከል ከጊዮርጊስ አደባባይ እስከ አዲሱ ገበያ ያለው አስፓልት የመንገድ አካፋይ ግንባታን መጥቀስ ይቻላል።

ስለ ጉዳዩ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የአካባቢው ነዋሪዎችና በግንባታው ላይ እየተሳተፉ ያሉ ወጣቶች ድርጊቱ የሕዝብና የመንግስት ገንዘብ ያለአግባብ እየባከነ እንደሆነ ያሳያል ይላሉ።

በየጊዜው እየፈረሱ በሚገነቡ የመንገድ አካፋይ ጉብታዎች ሳቢያ እግረኞች ለአደጋ ይጋለጣሉ፣ የትራፊክ ፍሰት ይስተጓጎላል፣ የአቅመ ደካሞችና አካል ጉዳተኞች እንቅስቃሴ ላይም እክል ይፈጠራል ሲሉ ገልጸዋል።

ይህ ብቻም አይደለም በአስፓልት መንገዶች አካፋይ ላይ በየወቅቱ የሚተከሉ ዛፎች እድገት እየተገታ መሆኑንም ጠቁመዋል።

እንደ ነዋሪዎቹ ገለጻ ይህ የመንገድ አካፋይ ዓመት ሳይሞላው ለሁለተኛ ጊዜ እየተገነባ ነው።

ከፍተኛ ገንዘብ ወጥቶባቸው የሚሰሩት የመንገድ አካፋይ ፕሮጀክቶች ለረጅም ጊዜ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ በቅድሚያ ጥናት ሊደረግ ይገባል ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በማኅበር ተደራጅተው የመንገድ አካፋይ ስራ ላይ የተሰማሩት ወጣቶችም አሁን የሚሰሩት የመንገድ አካፋይ ቀደም ሲል ከነበረው በቁመትም ሆነ  በመጠን የተለየ መሆኑን በመግለጽ ለውበትም ሆነ አደጋን ለመቆጣጠር የሚያስችል መሆኑን ይናገራሉ።

የግንባታ ውል ስምምነቱን በ2011 ዓ.ም ነሐሴ መጨረሻ መፈራረማቸውን የገለጸውና በግራር ኮንስትራክሽን ተደራጅቶ የሚሰራው ወጣት ታደሰ አየለ አሁን እየተሰራ ያለው ስራ ጥራቱን የጠበቀ በመሆኑ ለዘለቄታው የሚያገለግል ነው ብሏል።

ይሁን እንጂ  ስራ መፍጠር ከሚለው እሳቤ ባሻገር ግንባታው ዓመት ሳይሞላው ከሚለወጥና የአገር ሃብት ከሚባክን ታስቦበት በጥናት ቢሰራ መልካም ነው ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።

ለመዲናዋ ውበት አዳዲስ ዲዛይኖች እንደሚያስፈልጉ የገለጸው አበባው ኃይሉም ጥርት ያለ ነገር ተሰርቶ በተሻለ መንገድ ለረጅም ጊዜ እንዲያገለግል መደረግ አለበት ይላል።

የስራው ባለቤት የሆነው የአዲስ አበባ  የተፋሰስና አረንጓዴ  አካባቢዎች ልማት አስተዳዳር ኤጀንሲ ስለ ጉዳዩ በስልክ እና በደብዳቤ በተደጋጋሚ ቢጠየቅም ምላሽ ለመስጠት ፍቃደኛ አልሆነም።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም