በማህበራዊ ሚዲያ መልካም አስተሳሰብን በመስበክ ለዘላቂ ሰላም መጠቀም ይገባል----በመቀሌ ምሁራንና ባለሙያዎች

101
መቀሌ (ኢዜአ) ህዳር 18 ቀን 2012 ዓ.ም--- በማህበራዊ ሚዲያ የሚለቀቅ መረጃ መልካም አስተሳሰብን የሚሰብክና ስርዓትን የተከተለ በማድረግ ለዘላቂ ሰላም መጠቀም ይገባል ሲሉ አንድ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ምሁርና ሌሎች ባለሙያዎች ገለጹ። በዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መምህርና ተመራማሪ አቶ ተስፋይ ገብረመስቀል ለኢዜአ እንዳሉት፣ በዓለም ላይ ከሚገኘው 7 ቢሊዮን ህዝብ መካከል 3 ነጥብ 4 ቢሊዮን የሚሆነው የማህበራዊ ሚድያ ተጠቃሚ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥም ተንቀሳቃሽ የስልክ አገልግሎት ከሚጠቀመው 68 ነጥብ 34 ሚሊዮን ህዝብ መካከል 5 ነጥብ 6 በመቶ የሚሆነው የማህበራዊ ሚድያ ተጠቃሚ መሆኑንም አቶ ተስፋይ ተናግረዋል። በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ኢንተርኔት፣ ቲዊተርና ፌስቡክ ከሚጠቀሙ ሰዎች ውስጥ 70 በመቶ ያህሉ ከ25 እስከ 35 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች መሆናቸውን ገልጸዋል። እንደ መምህር ተስፋይ ገለጻ ከተገልጋዮች አጠቃቀም አንጻር ሲታይ አንድ ሰው በተጭበረበረ መንገድ እስከ አምስት የፌስ ቡክ አካውንቶችን ከፍቶ ሲጠቀም ይስተዋላል። “በቁጥር ወይም በመቶኛ ትክክለኛውን አሀዝ ማስቀመጥ ባይቻልም በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ማህበራዊ ሚድያ የሚጠቀሙ ሰዎች በአብዛኛው ሁከትና ግርግርን የሚሰብኩ እና ለግጭት የሚያነሳሱ መልዕክቶችን የሚያሰራጩ ናቸው” ብለዋል። የሚሰራጩ የተዛቡ መልዕክቶች ለብርካታ ንጹሀን ዜጎች ሕይወት ማለፍና ለከፍተኛ ንብረት መውደም መንስኤ እየሆኑ መምጣታቸውንም ተናግረዋል። “በማህበራዊ ሚዲያዎች ሰላም፣ የህዝቦች ፍቅርና መልካም እሴቶችን ከመስበክ ይልቅ በየቦታው ግጭቶች እንዲነሱ በትኩረት ስለሚሰራ ለሰላም እጦት ምክንያት እየሆኑ መጥተዋል” ብለዋል። በመሆኑም ማህበራዊ ሚድያ የሚጠቀም ሰው የፅሁፍ፣ የፎቶ፣ የቪድዮና መሰል መልዕክቶችን ከማሰራጨቱ በፊት ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት መመርመርና ጥቅሙና ጉዳቱን ማመዛዘን እንዳለበት አስገንዝበዋል። በተመሳሳይ የመልዕክቱ ተጠቃሚዎችም ይዘቱን በሚገባ በመመርመርና እውነታውን በማጣራት ሊቀበሉት እንደሚገባ ነው የገለጹት። የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ከጥፋት ይልቅ ሰላም፣ የህዝቦችን አንድነትና ፍቅር የሚሰብኩ መልዕክቶችን ለማስተላለፍ እንዲጠቀሙበትም መክረዋል። በማህበራዊ ሚዲያው ሥርአት ጠብቆ መልካም አስተሳሰሰቦችን ማስረጽ ከተቻለ ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ አይነተኛ መሳሪያ ሆኖ ሊያገለግል እንደሚችልም አቶ ተስፋይ ተናግረዋል። ''በማህበራዊ ሚዲያዎቹ የሚተላለፉ መልእክቶች ሁልጊዜ እውነት ናቸው ብሎ መቀበል አግባብ እይደለም ''ያሉት ምሁሩ፣ መልእክቶቹ ማን እንደላካቸውና ለምን ዓላማ እንደተላኩ ከተለያዩ አቅጣጫዎች መዝኖ ማየት እንደሚገባ ጠቁመዋል። በመንግስትና በግል ተቋማት የሚሰሩ በርካታ ሠራተኞች ህዝቡን በቅንነት ከማገልገል ይልቅ ጊዜያቸውን ማህበራዊ ሚዲያዎቹን በመጠቀም እንደሚያሳልፉ የገለጸው ደግሞ ጋዜጠኛ ሐጋዚ ወልዱ ነው። ብዙዎችም ኃላፊነት በጎደለው መልኩ በዜጎች መካከል ግጭት የሚያስነሱ መልዕክቶችን እንደሚያስተላልፉም ጠቁሟል። “ማህበራዊ ሚዲያ ካለው ሰፊ ተደራሽነትና አሁን ካለው ተቀባይነት ለዓለም ሰላም፣ ለልማትና እድገት መጠቀም ይቻላል” ያሉት ደግሞ በፌደራል እንባ ጠባቂ ተቋም የመቀሌ ቅርጫፍ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ዘርኡ ገብረመስቀል ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም