በጉጂ ዞን ከተተከሉ 74 ሚሊዮን ችግኞች መካከል 79 በመቶ የሚሆኑት ፀድቀዋል

71

ነገሌ ኢዜአ ህዳር 19 ቀን 2012 በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ባለፈው ክረምት ከተተከሉት 74 ሚሊዮን ችግኞች መካከል 79 በመቶ የሚሆኑት መፅደቃቸውን የዞኑ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ገለጸ

በጽህፈት ቤቱ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ባለሙያ አቶ ወንዶ ሸርቦቴ እንደገለፁት በዞኑ ባለፈው ክረምት 74 ነጥብ 7 ሚሊዮን ችግኝ መተከሉን ገልጸዋል፡፡

በተከላው 181 ሺህ የአካባቢው ነዋሪዎች የተሳተፉ ሲሆን በአረንጓዴ አሻራ ቀን ብቻ በአንድ ጀንበር 4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ችግኝ ተተክሎ እንደነበር አስታውሰዋል።

በዞኑ 14 ወረዳዎች በተደረገ ክትትልና የመስክ ጉብኝት 56 ነጥብ 2 ሚሊዮን ችግኝ ሙሉ በሙሉ መጽደቁን ተረጋግጧል ።

የጸደቁትን ችግሮች የዞኑ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች በማረም ፣ በመኮትኮትና ውሀ በማጠጣት እንክብካቤና ጥበቃ እያደረጉለት መሆኑን ባለሙያው ገልፀዋል ።

የዞኑ ህዝብ አረንጓዴ ልማትን ለማስፋፋት ችግኞችን ከመትከል እስከ በመንከባከብ እያደረገ ላለው ጥረትም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በሊበን ወረዳ የድቤ ጎቼ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሳራ መቃሳ በሰጡት አስተያየት በአካባቢያቸው የነበረው የተፈጥሮ ደን በመጨፍጨፉ ለድርቅ ተጎጂነት እንዳጋላጣቸው ተናግረዋል ።

ባለፉት ሁለት አመታት የተከሰተው ድርቅ ደግሞ ችግኝ መትከልና መንከባከብ ብቸኛው አማራጭ መሆኑን አስተምሮን አልፏል ብለዋል፡፡

ባለፈው ክረምት ለተተከሉ ችግኞች በሳምንት ሶስት ቀን ከአካበቢያቸው ነዋሪዎች ጋር በየተራ ውሀ እያጠጡና እየተንከባከቡ እንደሚገኙ አውስተዋል ።

ሌላው የወረዳው ነዋሪ ወይዘሮ ቀበሌ ጎዳና ድርቅን ለመከላከል ችግኝ በመትከል አረንጓዴ ልማትን ማስፋፋት የውዴታ ግዴታ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ቀደም ባሉት አመታት በተፋሰሶች አካባቢ የተተከሉ ችግኞች የተራቆቱ መሬቶችን ወደ ቀደመ ለምነት መመለሳቸውን በተግባር አይቻለሁ ያሉት ወይዘሮ ቀበሌ የአካባቢ ጥበቃ ስራው አጠናክረን እንቀጥልበታለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም