በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን 430 ሺህ 782 ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ይሰማራሉ

96
ደብረ ብርሃን ሰኔ 14/2010 በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በክረምት ወራት 430 ሺህ 782 ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለማሳተፍ የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ አስታወቀ። በመምሪያው የወጣቶች ጉዳይ ማካተት ንቅናቄና ተሳትፎ ቡድን መሪ ወይዘሮ እመቤት ጌታሁን እንደገለጹት ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ኮሌጆችና ከ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለእረፍት ወደ ቤተሰቦቻቸው የሚመለሱ ወጣቶች በሥራው ይሳተፋሉ። በእዚሀም ወጣቶቹ ማህበረሰብ ልማት ተኮር በሆኑ በጤና፣ በግብርና፣ በትምህርት፣ በአካባቢ ጽዳት፣ በመንገድ ስራና በሌሎች ዘርፎች እንደሚሳተፉ አመልክተዋል። ወይዘሮ እመቤት እንዳሉት በልማት ሥራው ከሚሳተፉት ወጣቶች መካከልም 172 ሺህ 334 የሚሆኑት ሴቶች ናቸው። ለስራው ስኬታማነት የሚመለከታቸው ባለድርሻ ተቋማት ቀድመው እቅዶችን በማውጣትና አስፈላጊ መሳሪያዎችን በማቅረብ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ገልፀዋል። ወይዘሮ እመቤት እንዳሉት በመጠናቀቅ ላይ ባለው የበጋ ወራት 84 ሺህ 900 ወጣቶች ደም የመለገስ፣ የአቅመ ደካማ ሰዎችን ቤቶች የመጠገን፣ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና መሰል ተግባራት ሲያከናውኑ ቆይተዋል። ወጣቶቹ በበጋው ባከናወኑት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን የሚገመት የጉልበት አስተዋጽኦ ማበርከት እንደቻሉ ገልጸው፣ በእዚህም 47 ሺህ 529 ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ ተናግረዋል። በደብረ ብርሃን ከተማ የ11ኛ ክፍል ተማሪ ሒሩት ፍቅሬ በበኩሏ ባለፈው ዓመት በአካባቢ ውበት ሥራና የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባር መሳተፏን አስታውሳለች። ባከናወነችው ሥራም በገንዘብ የማይገመት የመንፈስ እርካታ ማግኘት እንደቻለች አስታውሳ፣ በዘንድሮ ክረምትም የእረፍት ጊዜዋን በመጠቀም የበጎ ፈቃድ ሥራዋን አጠናክራ ለመቀጠል መዘጋጀቷን አስታውቃለች። በዞኑ ባለፈው የክረምት ወቅት በተካሄደ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 299 ሺህ 600 ወጣቶች ተሳትፈው ከ179 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የጉልበት አስተዋጽኦ ማበርከት መቻላቸው ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም