በደን ሃብት አጠባበቅና ችግሮቹ ዙሪያ በማይጨው ከተማ ውይይት ተካሄዷል

123
ማይጨው ሰኔ 14/2010 በተለያየ ምክንያት እየተመነጠረ ያለውን የተፈጥሮ ደን እንዲያገግም የበኩላቸውን እንደሚወጡ የትግራይ ደቡባዊ ዞን አንዳንድ አርሶ አደሮች ተናገሩ። በደን ሃብት አጠባበቅና ችግሮቹ ዙሪያ ትናንት በማይጨው ከተማ ውይይት ተካሄዷል። በውይይቱ ላይ የራያ አዘቦ ወረዳ አርሶአደር አህመዲን አረቦ እንዳሉት በአከባቢያቸው ለተፈጥሮ ደን ልማትና ጥበቃ የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ ነው። በመሆኑም እድሜ ጠገብ በሆኑ የተፈጥሮ ዛፎች ላይ የሚደርሰው ጉዳት በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡ እንዲሁም “ከተተከሉ ገና 10 ዓመት ያልሞላቸው የደን ሃብቶች በህገ ወጥ መንገድ እየተቆረጡ ለማገዶነት እየዋሉ በመሆናቸው ሁኔታውን አሳሳቢ አድርጎታል''  ብለዋል አርሶአደር አህመዲን። ‘‘እኔ ከብትም ሆነ ግመል አስሮ በመቀለብ ድርሻዬ እየተወጣሁ ነኝ ‘‘ያሉት አርሶአደር አህመዲን፣ እየተፈጸመ ያለውን ህገ ወጥ የደን ጭፍጨፋ ለመግታት የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ሌላው የዚሁ ወረዳ አርሶአደር አድሃና ሓዲስ እንዳሉት፣ እሳቸውን ጨምሮ የአካባቢው  አርሶ አደሮች በየአመቱ ችግኝ በመትከል እያለሙ ነው። ቢሆንም በዞኑ ውስጥ በግብርና ኢንቨስትመንት ምክንያት የተተከለው ችግኝ እየተመነጠረና በየጊዜው እየተመናመነ መምጣቱን ገልፀዋል፡፡ “ከተጎራባች አከባቢ የሚመጡ ግለሰቦች በደን ክልል ወስጥ ህገ ወጥ የንብ እርባታ በማካሄዳቸውና የማር ምርትን ለመቁረጥ በሚጠቀሙት እሳት የተፈጥሮ ደን ላይ ውድመት እያስከተለ ነው'' ያሉት ደግሞ በዞኑ የእንዳመሆኒ ወረዳ አርሶአደር ይባስ ይብራሕ ናቸው። ጉዳቱን ለመከላከል ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን የገለፁት አርሶ አደሩ፣ የሚመለከታቸው አካላትም የአርሶ አደሮቹ ጥረት ሊደግፉ እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡ በስፋት የጫት ተክል የሚያለሙ  አርሶአደሮች እየተበራከቱ መምጣቱ ለደን መመንጠር ምክንያት መሆኑን የሚናገሩት ደግሞ የዚሁ ወረዳ የግብርና ባለሙያ አቶ ጣዕመ ከበደ ናቸው። የራያ አዘቦ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ጉዑሽ ሃይሉ በበኩላቸው በደን ሃብት ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ግለሰቦችን ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የመከላከል ስራው ስኬታማ ለማድረግም የዞኑ ህዝብ የደን ሃብት መመናመን የሚያስከትለውን ጉዳትና በመከላከል ዘዴዎች ላይ የግንዛቤ ትምህርት እየተሰጠው መሆኑን ተናግረዋል። በማይጨው ከተማ ትናንት በተካሄደው ውይይት ላይ ከዞኑ ስምንት ወረዳዎች የተውጣጡ አንድ ሺህ ያህል አርሶአደሮች፣ የግብርና ባለሙያዎችና የወረዳ አመራር ኣካላት ተሳትፈዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም