የኮሙኒኬሽንና ሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ማሕበር ተመሰረተ

69
ህዳር 18/2012የኢትዮጵያ የኮሙኒኬሽንና ሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ማሕበር ዛሬ በአዲስ አበባ በይፋ ተመሰረተ። በአገር አቀፍ ደረጃ የተመሰረተው ማሕበሩ የኮሙኒኬሽንና ሕዝብ ግንኙነት ሙያ መርሆችን መሰረት በማድረግ የሚንቀሳቀስ መሆኑ ተገልጿል። የማሕበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ደምሰው በንቲ የማሕበሩ መመስረት ባለሙያዎች የሚጠበቅባቸውን ሙያዊ ግዴታ በአግባቡ እንዲወጡ ያስችላል ብለዋል። ማሕበሩ የዘርፉ ባለሙያዎች በአገሪቷ ልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ለማድረግ ያግዛልም ነው ያሉት። በዓለም አቀፍ ተቋማት፣ በመንግስት የፌደራልና የክልል ተቋማት፣ በግልና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶችና በሌሎች ተቋማት የሚሰሩ ባለሙያዎች የማሕበሩ አባል እንዲሆኑም ጥሪ አስተላልፈዋል። የማሕበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ወንድም ተክሉ በበኩላቸው በአገሪቷ የሕዝብ ግንኙነት ሙያ ሕዝብና መንግስት የሚፈልገውን ያህል ርቀት ከመሔድ አኳያ ክፍተቶች ነበሩበት ብለዋል። በመሆኑም ማሕበሩ በመንግስትም ሆነ በግሉ ዘርፍ የተሰማሩ ግለሰቦችን በማቀፍ ሙያቸውን ብቻ መሰረት አድርገው እንዲቀሳቀሱ ለማድረግ እንደሚሰራ ገልጸዋል። ማህበሩ በአገር ውስጥ በዘርፉ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ከሚሰጡ የትምህርት ተቋማት ጋር የሚሰራ ሲሆን ከአገር ውጪም ተመሳሳይ ግንኙነቶችን እየፈጠረ መሆኑን አውስተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም