በይርጋጨፌ ወረዳ አርሶ አደሮች በቡና ልማት ያላቸውም መልካም ተሞክሮ ለሌሎች አካፈሉ

105

ኢዜአ ህዳር 18 / 2012 በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ወረዳ አርሶ አደሮች በቡናና ቅመማ ቅመም ችግኝ ዝግጅት አንስቶ እስከ ምርት አሰባሰብ ድረስ ያላቸውን መልካም ተሞክሮ ለሌሎች አካፈሉ።

አርሶ አደሮቹ ተሞክሯቸውን ያካፈሉት  ከህዳር 16/2012 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ቀናት በይርጋጨፌ ወረዳ የለማ ቡናና  ቅመማ ቅመም በመስክ ጉብኝት በተካሄደበት ወቅት ነው።

በመስክ ጉብኝቱ ከዞኑ ሁሉም ወረዳዎች የተወጣጡ 200 አርሶ አደሮች ተካፋይ ሲሆኑ የፌዴራል፣ የክልል እና የዞኑ ስራ ኃላፊዎችና የዘርፉ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

ተሞክሯችውን ካከፈሉት የይርጋጨፌ ወረዳ አርሶ አደሮች  መካከል ሲሳይ ኤሌማ በሰጡት አስተያየት በአንድ ተኩል ሄክታር የቡና ማሳቸው ላይ ባከናወኑት የቡና ጉንደላ /እድሳት/ ስራ ምርታማነት ከእጥፍ በላይ መጨመሩን ገልጸዋል።

ቡናቸው ማርጀቱን ተከትሎ የምርት መጠኑም ሆነ ጥራቱ እየወረደ በመምጣቱ ያደሱት ባለፉት ሶሰት ዓመት ካላቸው ሶስት ሄክታር ውስጥ  ነው።

እድሳት የተደረገበት ቡና በዓመቱ ምርት መስጠት መጀመሩንም ጠቁመዋል።

ከዚህ ቀደም ያገኙት የነበረው ምርት በሄክታር ከአስር  ኩንታል የማይበልጥ የነበረው  በተያዘው የምርት ዘመን በመጀመሪያ ዙር ለቀማ ብቻ በሄክታር ከ11 ኩንታል በላይ መሰብሰብ እንደቻሉ ገልጸዋል።

ይህም ከመጎንደሉ በፊት ከሚገኝው ምርት ጋር ሲነጻጸር ብልጫ ያለው ምርት እንዳገኙ አስረድተዋል።

አርሶ አደር ሙሉጌታ ከበደ በበኩላቸው የቡና ማሻሻያ ፓኬጅን ተግባራዊ በማድረግ ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለዓለም ገበያ በማቅረም አምና ከ400 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

ከችግኝ ጣቢያዎች ዝርያቸው የተለየና የተሻሻሉ የቡና ችግኞችን በመውሰድ የአፈር ማዳበሪያና የቁፋሮ ዝግጅት በአገባቡ በማከናወን የተከሏቸው ችግኞች ሁሉም ጸድቀው በአንድ ዓመት ውስጥ ማበባቸውን ጠቁመዋል።

ከዚህ በፊት በልማዳዊ አሰራር የሚተክሏቸው ችግኞች ብዙዎቹ ከመድረቃቸው ባለፍ የመጀመሪያ ዙር አበባ የሚያሳዩት ከሶስት ዓመታት በኋላ እንደሆነ አመልክተዋል።

ከሌላ ወረዳ የመጡት አርሶ አደር ደግፌ ዋታ እንዳሉት ከዚህ ቀደም በመደብና በጫካ ውስጥ የሚያፈሉት የቡና ችግኝ የመጽደቅ  መጠኑ ከግማሽ  በታች ነው።

ምርት ለመስጠት  ከአራት ዓመት በላይ እንደሚያስጠብቅ፣ በበሽታና በተባይ የመጠቃት እድላቸው ሰፊ መሆኑን ጠቁመዋል።

በልምድ ልውውጡ በችግኝ ዝግጅትና ምርት አሰባስብ ዙሪያ የወሰዱትን ልምድ በመጠቀም በማሳቸው ውስጥ የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ  ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል

የዞኑ  እርሻና ተፈጥሮ ሃብት መምሪያ ኃላፊ አቶ ተገኝ ታደሰ  በተያዘው ዓመት ከ25 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዞኑ የቡና ጥራት ለመጠበቅ በተለይ ከልማዳዊ የችግኝ ዝግጀት በመላቀቅ የተሻሻሉ ዝርያዎችን የማላመድ ስራ እየተከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል።

ከቡና ልማት በተጓዳኝ  በአርሶ አደሩ ማሳ ዝንጅብል ፣ኮረሪማና ሌሎችንም ቅመማ ቅመሞችን በማላመድ አማራጭ የገቢ ምንጭ በመፍጠር ላይ እንደሚገኙ አመልክተዋል።

የደቡብ ክልል ቡና ሻይና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ኃላፊ አቶ መስፍን ቃሬ እንደገለጹት በቡና ልማት የተገኙ መልካም  ተሞክሮዎችን ወደ ሁሉም አርሶ አደሮች በማስፋት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ ይሰራል።

በተለይ የቡና ጥራትንና ጣዕምን ጠብቆ በማቆየት ከዘርፉ የሚገኘውም ጥቅም ለማጎልበት በትኩረት መሰራት እንዳለበት ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም