በጎንደር የቱሪስት ቆይታን በማራዘም ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው

99
ኢዜአ ህዳር 17/2012 በጎንደር ከተማ የሚገኙ መስህቦችን ለመጎብኘት የሚመጡ ቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜን በማራዘው ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የከተማዋ አስተዳደር አስታወቀ፡፡ የከተማዋ አስተዳደር የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት እቅድና የደረሰበት ደረጃ ግምገማ ዛሬ ተካሂዷል፡፡ የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ  አቶ በሪሁን ካሳው በግምግማው መድረክ እንዳሉት ጎንደር በርካታ የቱሪስት መዳረሻ ፣  ባህላዊና ኃይማኖታዊ ቅርሶች  መገኛ ከተማ ናት ። ሆኖም አሁን ላይ ያለው የጎብኚዎች  አማካይ የቆይታ ጊዜ ከአንድ ቀን ተኩል  በታች መሆኑ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም አሟጦ መጠቀም እንዳልተቻለ ተናግረዋል። በዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም በማሳደግ የከተማ ነዋሪውን ኑሮ ለማሻሻል እንዲረዳ  ቱሪስቶች የቆይታ ጊዜን ወደ ሁለት ቀን ከግማሽ እንዲራዘም መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ በከተማዋ የሚሰጡ የሆቴል፣ የትራንስፖርትና የአስጎብኝ አገልግሎትን በማሻሻል አለማቀፋዊ ደረጃን የጠበቁ እንዲሆኑ በማድረግ ለጎብኝዎች ተመራጭ ከተማ ለማደረግ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ "የቅርስ ጥበቃና ባህላዊ መስህብ ሀብቶችን ማስፋት፣ ጉዳት የደረሰባቸውን ቅርሶች ታሪካዊ ይዘታቸውን በጠበቀ መልኩ መጠገንና ያሉን የቱሪስት ሀብቶችን የማስተዋወቅ ስራ ሊሰራ ይገባል" ብለዋል። በተለይም ጎንደር ከምትታወቅባቸው የፋሲል ቤተመንግስት፣ አብያተ ቤተክርስቲያንና ገዳማት በተጨማሪ ሌሎች ቅርሶችን በማጥናትና በማልማት የማስተዋወቅ ስራ ትኩረት መሰጠት እንዳለበት አሳስበዋል። የጎንደር ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አስቻለው ወርቁ በበኩላቸው በከተማዋ ያሉ ቅርሶች ጠብቆ ለመንከባከብ  የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ኃላፊው እንዳመለከቱት ቱሪስቶች ላይ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ተቋማትን በመለየት የማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድ ምክር ቤቱ ይሰራል። በከተማዋ በጣሊያን ወረራ ወቅት የተገነቡ 74 ክብ ቤቶችንም በመጠገን ከተማዋን ማራኪና ሳቢ እንደሚደረግም ጠቅሰዋል፡፡ የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤቱ ዓላማ ለቅርሶች ጥበቃና እንክብካቤ ተብሎ የተመደበ በጀትን የመከታተልና በቅርሶች ላይ የሚታዩ ችግሮችን በመለየት መፍትሄ ማምጣት እንደሆነ ገልጸዋል። ምክር ቤቱ ለተያዘው የበጀት ዓመት ማስፈጸሚያ የሚውል አስር ሚሊዮን 700ሺህ ብር አጽድቋል። ምክር ቤቱ በጎንደር የተቋቋመው በ2010 ዓ.ም ቢሆንም በአካባቢው በነበረው የጸጥታ ችግር  የሚፈለገውን ያህል መንቀሳቀስ ሳይችል መቆየቱ ተወስቷል። በከንቲባው የሚመራና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በአባልነት የሚገኙበት ምክር ቤት ሲሆን የበጀት ወጪው የሚሸፈነው ከከተማ አስተዳደሩና ከመስህብ  እንዲሁም ከሌሎች የገቢ ምንጮች  እንደሆነ ተመልክቷል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም