የንግድ ትርዒቶች፣ኤግዚቢሽንና ባዛሮችና ጉልህ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እያስገኙ ነው

110
አዲስ አበባ ሰኔ 14/2010 በከተማዋ የሚካሄዱ የንግድ ትርዒቶች፣ ኤግዚቢሽንና ባዛሮችና በግሉ ዘርፍ የተሰማሩ አምራቾችና ነጋዴዎችን በማነቃቃት ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እያስገኙ መሆኑን የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አስታወቀ። ምክር ቤቱ ሁለተኛውን አለም አቀፍ አዲስ ቻምበር የንግድ ትርኢትና ባዛር ዛሬ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ከፍቷል። ኤግዚቢሽኑን በይፋ የከፈቱት የአዲስ አበባ የንግድ ዘርፍና ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ኤልያስ ገነቲ እንደተናገሩት፤ በየጊዜው የሚካሄዱ የንግድ ትርዒቶችና ኤግዚቢሽኖች በማምረት ዘርፍ ለተሰማሩ የግል አምራቾችና ነጋዴዎች ጥቅም እያስገኙ ነው። በዚህ ዛሬ በተከፈተው በሁለተኛው ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት፤ ባዛርና ኤግዚቢሽኖች አምራቾች ምርቶቻቸውን ለተጠቃሚዎች ለመሸጥና ለማስተዋወቅ ትልቅ እድል የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል። የአሁኑ የንግድ ትርዒት፣ ባዛርና ኤግዚቢሽን ላይ በርካታ የውጭ አምራች ድርጅቶችና ግለሰቦች የሚሳተፉበት መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ “ለአገር ውስጥ አምራቾች ልምድ ለመቅሰም ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል'' ብለዋል። ምክር ቤቱ የንግዱን ማህበረሰብ በማነቃቃትና ድጋፍ በማድረግ አገሪቱ በጀመረችው የእድገት ጎዳና ዋና ተዋናይ እንዲሆን ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። በተጨማሪም የተቀዛቀዘውን የውጭ ንግድ ማነቃቃትና  ትልቅ የስራ እድል መፍጠሪያ የሆነው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን ትኩረት እንዲያገኝ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል። በኤግዚቢሽኑ የካንጋሮ ጫማ ፋብሪካን ወክሎ የተገኘው ወጣት አብርሃም ክብሩና ከቃሊቲ ብረታብረት ፋብሪካ የመጡት ወይዘሮ ጽጌ መኮንን በበኩላቸው ተመሳሳይ ኤግዚቢሽንና ባዛሮች መካሄዳቸው በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለተሰማሩ አምራች ነጋዴዎች ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል። የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የማምረቻና መሸጫ ቦታዎች እጥረት ዘርፉ በሚፈለገው ልክ እድገት እንዳያመጣ እንቅፋቶች መሆናቸውን ተናግረዋል። በዚህም ተቀራርቦ በመስራት መንግስት ከአምራች ነጋዴ ማህበረሰብ ጋር በመሆን ለችግሮቹ መፍትሄ እየሰጠ መሄድ እንዳለበት አመልክተዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም