የዓድዋ ሪፈራል ሆስፒታል የማስፋፊያ ግንባታ ፕሮጀክት ከአንድ ዓመት በላይ ተጓቷል

120

ኢዜአ ህዳር 16 ቀን 2012 የዓድዋ ሪፈራል ሆስፒታል የማስፋፊያ ግንባታ ፕሮጀክት መጠናቀቅ ከነበረበት ጊዜ በላይ በመጓተቱ ምክንያት የተሟላ የጤና አገልግሎት ማግኘት እንዳልቻሉ የከተማው ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ገለጹ።

ግንባታውን የሚያከናውነው የዛምራ ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በበኩሉ በተሰጠው 600 የሥራ ቀናት ስራውን ጨርሶ ለማስረከብ ዝግጁ መሆኑን አመልክቷል።

የአድዋ ከተማ ምክር ቤት አባል አቶ ተሻለ መስፍን እንዳሉት የከተማው ህዝብ ለረዠም ዓመታት የመሰረተ ልማት ፍላጎት ጥያቄውን ሲያነሳ ቆይቷል።

በእዚህም የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመፍታት በተለያዩ ጊዜያት ከ20 በላይ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ለማከናወን የመሰረተ ድንጋይ ቢቀመጥም እስካሁን ድረስ የአንዳቸውም ግንባታ አለመጀመሩን አቶ ተሻለ ተናግረዋል።

"የፕሮጀክቶቹ ግንባታ መዘግየቱ በከተማው ህዝብ ላይ ቅሬታ አስከትሏል" ብለዋል።

አቶ ተሻለ እንዳሉት ከተጓተቱ የልማት ፕሮጀክቶች መካከል በ2008 ዓ.ም የማስፋፊያ ግንባታውን ተጀምሮ በ2011 ዓ.ም መጀመሪያ መጠናቀቅ ያለበት የአድዋ ሪፈራል ሆስፒታል ማስፋፊ ፕሮጀክት ነው።

እስካሁን ድረስ የተከናወነው የሪፈራል ሆስፒታሉ የማስፋፊያ ፕሮጀክት ግንባታ ሥራ ግማሽ ያህል ብቻ መሆኑንም አመልክተዋል።

የዓድዋ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ያለም በላይ በበኩላቸው የሆስፒታሉ ግንባታ መዘግየት አስመልክተው ቅሬታቸውን ለከተማው ምክር ቤት በተደጋጋሚ ቢያቀርቡም መፍትሄ አለማግኘታቸውን ተናግረዋል።

ይህም በተለይ ሴቶች፣ ህጻናት እና አቅም የሌላቸው አረጋዊያን ተገቢውን የህክምና አገልግሎት በቅርበት እንዳያገኙ እንቅፋት መፍጠሩንም ገልጸዋል።

የሚመለከታቸው አካላት ግንባታ እንዲፋጠን በማድረግ አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጧቸውም ጠይቀዋል።

አቶ ሐድጉ ገብረሚካኤል የተባሉት ሌላው የከተማው ነዋሪ በበኩላቸው "ስለሆስፒታሉ ግንባታ መጓተት አስመልክቶ ከህብረተሰቡ በየደረጃው ለሚገኙ መንግስታዊ አካላት ጥያቄ ቢቀርብም አስካሁን ድረስ አጥጋቢ ምላሽ አልተገኘም" ብለዋል።

ላለፉት 84 ዓመታት አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የዓድዋ ሪፈራል ሆስፒታል በአሁኑ ወቅት የሚጠበቅበትን የጤና አገልግሎት መስጠት ባለመቻሉ የከተማው ህዝብ ወደ አክሱምና መቀሌ ከተሞች በመሄድ የህክምና አገልግሎት ለማግኘት መገደዱንም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።

በከተማው ነዋሪዎች የቀረበው ቅሬታ ትክክል መሆኑን አምነው የተቀበሉት የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ከንፈ ገብረእግዚአብሔር ናቸው።

የሆስፒታሉ ግንባታ ባለፈው ዓመት መጀመሪያ ላይ መጠናቀቅ ሲገባው እስካሁን ድረስ የተከናወነው 51 በመቶ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል።

ሆስፒታል ከዓድዋ ከተማ ህዝብ ባለፈ በአምስት ወረዳዎች ለሚኖሩ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዜጎች ጭምር የጤና አገልግሎት እንዲሰጥ ታሳቢ ተደርጎ የዲዛይን ማሻሻያ ሥራ በመሰራቱ ምክንያት ግንባታው መጓተቱን ጠቁመዋል።

" የማስፋፊያ ግንባታ ፕሮጀክቱ ባለሁለት ፎቅ ሕንጻ ያለው ሲሆን ግንባታው ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር 160 አልጋዎችና 82 ሌሎች አገልግሎት መስጪያ ክፍሎች እንደሚኖሩት ሥራ አስኪያጁ አመልክተዋል።

በትግራይ ክልል ኮንስትራክሽን፣ መንግድና ትራንስፖርት ቢሮ የህንጻ ዲዛይን ዳይሬክተር አቶ ክፍለስላሴ ጸጋይ በበኩላቸው ከዲዛይን ማሻሻያ በተጨማሪ የኢንዱስትሪ ምርት ውጤቶች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር ለፕሮጀክቱ መጓተት ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።

የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ የምህንድስና ባለሙያ አቶ ሰሎሞን ገብረስላሴ በበኩላቸው፣ "የተጓተተውን ግንባታ በማፋጠን የተገልጋዩን እንግልትና የጤና አገልግሎት ችግር ለመፍታት በትኩረት እንሰራለን " ብለዋል።

የግንባታ ፕሮጀክቱን ፈጥኖ ወደሥራ ለማስገባት ከከተማው ህዝብና ከህንጻ ተቋራጩ ጋር በቅንጅት ለመስራት መዘጋጀታቸውንም ባለሙያው ጠቁመዋል።

ለሆስፒታሉ ማስፋፊያ ስራው ከ280 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚስፈልግና እስከ አሁን ድረስ ለተከናወነው ስራ 120 ሚሊዮን ብር ክፍያ መፈጸሙን አመልክተዋል።

የቀሪው 49 በመቶ የሆስፒታሉ ግንባታ ሥራን በ600 የሥራ ቀናት ውስጥ ለማጠናቀቅ ሰሞኑን ከስራ ተቋራጩ ጋር ስምምነት ላይ መደረሱንም አቶ ክንፈስላሴ ተናግረዋል።

"መንግስት በውሉ መሰረት የዲዛይን ማስተካኪያ አድርጎ ከተዘጋጀና ቀሪ ክፍያውን በወቅቱ ከፈፀመ ከተባለው ጊዜ በፊት ሰርተን ለማስረከብ ዝግጁ ነን" ያሉት ደግሞ የማስፋፊያ ፕሮጀክቱን የሚያከናውነው ዛምራ ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ አብራሃም አሰፋ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም