ማስተካከያ የተደረገበት የረጲ/ቆሼ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ቦታ ማህበረሰቡ ላይ ሲደርስ የነበረውን ችግር ቀንሶታል ተባለ

145
ኢዜአ ህዳር 17 ቀን 2012 ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ማስተካከያ የተደረገበት የረጲ/ቆሼ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ቦታ ማህበረሰቡ ላይ ሲደርስ የነበረውን ችግር እንደቀነሰው ተገለጸ። አካባቢው ሙሉ በሙሉ ፅዱ እንዲሆን በቀጣይ በትኩረት መሰራት አለበትም ተብሏል። የተባበሩት መንግስት ድርጅት የህዝብ አሰፋፈር መርሃ ግብር (ዩኤን ሀቢታት) ዋና ዳይሬክተር ሚስ ማይሙናህ ሞሃድ ሻሪፍ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ ባለስልጣናትና የጃፖን አምባሳደር ዳይሱኬ ማትሱናጋ የተመራ ልዑካን ቡድን በረጲ/ቆሼ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ቦታ የተተከሉ ችግኞችን ትናንት ጎብኝተዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ረጲ በተለምዶ ቆሼ የሚገኘውን የቆሻሻ ማስወገጃ ስፍራ በአካባቢ ላይ ተፅእኖ እንዳይፈጥር እንዲሁም የማስወገጃ ስፍራውን በአግባብ ለመጠቀም የሚያስችል ፉኩካ የተሰኘ ፕሮጀክት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ መተግበር መጀመሩ ይታወሳል። ይህ ፕሮጀክት ከተማ አስተዳደሩ ከዩኤን ሃቢታት እና ከጃፓን መንግስት ጋር በመተባበር በቆሼ አንድ ሄክታር መሬትን መልሶ ማልማት የሚያስችል ነው። ፉኩካ የተሰኘው ፕሮጀክት የመጀመሪያው ክፍል የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት መጋቢት 5 ቀን 2011 ዓ.ም መመረቁም ይታወቃል። ባለፈው ክረምት በረጲ ቆሻሻ ማስወገጃ  13 ሺህ ችግኞች መተከላቸውም ተት። የዛሬው ጉብኝት ዓላማም የፉኩ ፕሮጀክት የተተከሉ ችግኞችን ያሉበትን ደረጃ መመልከት ነው። የአዲስ አበባ ከተማ የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ኤጀንሲ ስራ አስኪያጅ ዶክተር እሸቱ ለማ የፉኩካ ቴክኖሎጂ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃው ማህበረሰቡ ላይ ሲያደርሰው የቆየው ችግር እንደቀነሰው ገልጸዋል። በአካባቢው እጽዋቶች መተከላቸውና እርከን ተሠርቶ የሚንሸራተተውን ቆሻሻ ማስቆም እንደተቻለም ተናግረዋል። ባለፉት ወራት የተሰሩ ስራዎች የአካባቢውን ማህበረሰብ ከመጥፎ ሽታና ከህይወት መጥፋት ስጋት ማውጣት መቻሉ እንዳስደሰታቸውም አመልክተዋል። ዶክተር እሸቱ አክለውም በጃፖን መንግስት የተሰራው ቴክኖሎጂ የረጲ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ የከርሰ-ምድር ውሃ የአፈር ለምነት በመጠበቅ የወንዝ ውሃንና የአካባቢ አየር ብክለትን ለመከላከል ረድቷልም ብለዋል፡፡ በቀጣይም የቀሩ ስራዎችን በትብብር በመስራት የተሻለ አካባቢ ለመፍጠር ኤጀንሲው እንደሚንቀሳቀስም ነው ዶክተር እሸቱ የገለጹት። በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ዳይሱኬ ማትሱናጋ በበኩላቸው እንዳሉት በፉኩካ ቴክኖሎጂ ዘዴ ዘመናዊ የሆነ የቆሻሻ ማስወገጃ መሳሪያ በመትከል ከቆሻሻው የሚወጣውን መጥፎ ጠረን ወደ ጥሩ አየር የመቀየር ተግባር ተከናውኗል። የጃፓን መንግስት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር በቀጣይም የተሻለ ስራ በመስራት አካባቢው ፅዱና ማራኪ እንዲሆን እንደሚሰራ ገልጸዋል። የአካባቢው ነዋሪ ወይዘሮ ስርጉድ በዳዳ ለኢዜአ በሰጡት ቃል፤ ከዚህ በፊት ቆሻሻው ለህይወታቸው አስጊ እንደነበርና ከቆሻሻው የሚወጣው የተበከለ አየር ለተለያዩ በሽታዎች ሲያጋልጣቸው እንደቆየ ተናግረዋል። ፕሮጀክቱ ተግባራዊ ከሆነ በኋላ ግን የህይወትም የጤና ችግር የሚያመጣ ሽታ እንደሌለ ጠቅሰው  ቀሪ ስራዎች ተሰርተው ሙሉ በሙሉ ፅዱ የሆነ አካባቢ እንዲሆን ትብብሩ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ የቆሻሻ ማስወገጃው ቦታው ከከተማ አስተዳዳሩ 100 ሺህ ዶላር እና ከጃፖን መንግስት 2 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተደረገበት ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ ዩኤን ሀቢትም የቴክኖሎጂና የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርግም ተመልክቷል። ባለፈው ክረምት በረጲ ቆሻሻ ማስወገጃ  ከተተከሉት 13 ሺህ ችግኞች 85 በመቶው መጽደቁን ከአዲስ አበባ ከተማ የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በ2010 ዓ.ም በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ልዩ ቦታው "ቆሼ" እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የቆሻሻ ክምር ተደርምሶ በህይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሶ እንደነበር ይታወሳል። ባለፈው ዓመት ሰኔ 2011 ዓ.ም የቆሻሻው ክምር ዳግም ተደርምሶ በሰው ንብረት ላይ ጉዳት አድርሶም ነበር።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም