የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ወደ ዩጋንዳ አምርቷል

108

አዲስ አበባ ኢዜአ ህዳር 16 /2012 በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ የተመራ የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ዛሬ ከሰአት ወደ ዩጋንዳ አቅንቷል።

የፐብሊክ ዲፕሎማሲው የሁለቱን አገሮች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ማጠናከርን አላማ ያደረገ እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ የሚመራው የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ከ50 በላይ አባላትን የያዘ እንደሆነ ተገልጿል።

የልዑካን ቡድኑ ከምክር ቤቱ፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከሃይማኖት ተቋማት፣ ከታዋቂ ግለሰቦች፣ ከዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ ከኢትዮጵያ የንግድ ምክር ቤት፣ ከሴቶች የንግዱ ማህበረሰብ፣ ከስነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ ከሚዲያ ተቋማት፣ ከኢትዮጵያ የባህል ቡድን የተወከሉ አባላትን ያካተተ ነው።

የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድኑ በዩጋንዳ የአምስት ቀናት ቆይታ ይኖረዋል።

ቡድኑ በቆይታው ከፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሞሴቬኒ፣ ከዩጋንዳ ፓርላማ አፈ-ገባኤ፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ከማኬሬሬ ዩኒቨርሲቲ፣ ከዩጋንዳ ቱሪዝም ቦርድ፣ ከዩጋንዳ የሀይማኖት መሪዎች፣ ከዩጋንዳ የንግዱ ማህበረሰብ፣ ከኢትዮጵያ ኮሙዩኒቲ እና ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት ያደርጋል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ባህል ቡድንም የኪነጥበብ ፕሮግራም የሚያቀርብ ሲሆን የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድኑ በዩጋንዳ የሚገኙ ልዩ ልዩ ታሪካዊ ቦታዎችን እንደሚጎበኝም መግለጫው አመላክቷል።

ኢትዮጵያ እና ዩጋንዳ ግንኙነታቸውን የጀመሩት ኤድዋርድ ሙቴሳ በ1934 ዓ.ም በዩጋንዳ የቡጋንዳ ስርወ መንግስት ንጉስ ሆነው ቃል ኪዳን በፈጸሙበት ወቅት ቀዳማዊ ሀይለስላሴ በበዓለ ሲመታቸው ለመታደም ወደ ዩጋንዳ ከተጓዙበት ጊዜ ጀምሮ ነው።

ዩጋንዳ ኤምባሲዋን በ1962 ዓ.ም አዲስ አበባ የከፈተች ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ደግሞ በ1987 ዓ.ም በካምፓላ በቆንስላ ደረጃ የከፈተችውን ጽህፈት ቤቷን በኤምባሲ ደረጃ በማሳደግ ግንኙነቱ ተጠናክሯል።

በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ እና ዩጋንዳ ከሁለትዮሽ ግንኙነት ባለፈ ሁለቱም አባል በሆኑባቸው ዓለም አቀፍ መድረኮች ማለትም በሰሜን ኮርዲር የትስስር ፕሮጀክት፣ በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ)፣ በአፍሪካ ህብረት እንዲሁም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የሁለቱን አገሮች ህዝቦች ጥቅም ለማስከበር በትብብር በመስራት ላይ ይገኛሉ።

ከዚህ በተጨማሪ ሁለቱ አገሮች የናይል ተፋስስ አባል አገሮች በመሆናቸው የተፋሰሱ አገሮች አጠቃላይ የትብብር ማዕቀፍን በመፈረም እና በማጽደቅ ትብብሩ ተግባራዊ እንዲሆን ከሌሎች አባል አገሮች ጋር በትብብር በመስራት ላይ እንደሚገኙም የቃል አቀባይ ጽህፈት ቤቱ መረጃ ያመለክታል።

በተመሳሳይ የሱዳን ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ከህዳር 12 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ቀናት የኢትዮጵያና የሱዳን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የማጠናከር አላማ ያለው የሶስት ቀናት ጉብኝት በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጉ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም