በኢትዮጵያ ለዲጅታል ቤተ መጻህፍት ግንባታ ትኩረት ተሰጥቷል

82

ኢዜአ/ ህዳር 16 /2012 በኢትዮጵያ ሁሉም የተማረ ህብረተሰብ ሊጠቀምበት የሚችል ዲጅታል ቤተ መጻህፍት በመመስረት በእውቀትና ክህሎት የዳበረ ትውልድ ለመገንባት እየሰራ እንደሚገኝ የሳይንስ እና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር አስታወቀ።

በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቤተመዛግብትና ቤተ መጻህፍት ኤጀንሲ ከአማራ  ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮና ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በቤተመዛግብት መረጃ ማሰባሰብና ተያያዥ ችግሮች ላይ ያተኮረ ውይይት በባህርዳር ከተማ አካሔዷል።

በሚኒስቴሩ የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ተቋም ባለሙያ ወይዘሮ ዮርዳኖስ ግርማ እንዳሉት አለም አሁን ከደረሰበት የቴክኖሎጂ ምጥቀት ጋር እኩል ለመራመድ በአገር አቀፍ ደረጃ የዲጅታል ላይብረሪ በማቋቋም የመረጃን ልውውጡ ማፋጠን ይገባል።

በዚህም ተቋሙ በ2010 ዓ.ም የዲጅታል ቤተ መጻህፍት በማቋቋም፣ አሰራርና አደረጃጀት በመፍጠር ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በመግባት መረጃን ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የተቋሙ ዋና ዓላማም ለአገርና ለህዝብ የሚጠቅሙ መረጃዎችን ማሰባሰብ፣ በሳይንሳዊ መንገድ ወደ ኮምፕዩተር ማስገባት፣ ማከማቸትና በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ ለሚኖረው ማህበረሰብ ተደራሽ ማድረግን ያለመ ነው።

እስካሁን ተቋሙ ባደረገው ጥረትም ከ100 ሺህ በላይ መጻህፍት፣ የጥናት ስራዎችን፣መጽሄቶችና ሌሎች ሰነዶችን ወደ ዲጅታል ቤተ መጻህፍት በማስገባት ለተጠቃሚዎች ክፍት ማድረጉን አስረድተዋል።

በአገራችን የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችን፣ ቤተ መጻህፍትን፣ ቤተ መዛግብትንና ሌሎች በዲጅታል ቤተ መጻህፍት የሚሰሩ ተቋማትን ወደ ቋት በማምጣት በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የኢንፎርሜሽን ሳይንስ መምህር አቶ ጌታቸው ገዳሙ በበኩላቸው በአገራችን አሁን ላይ ምሁራን መጻህፍትን ከማንበብ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መጠቀምን እየመረጡ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

በዲጅታል ቤተ መጻህፍት ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጅን ተጠቅመው የሚደራጁና የሚለቀቁ መረጃዎች በቀላሉ ተደራሽ ማድረግ ለተመራማሪዎች፣ መምህራንና ተማሪዎች ጊዜን፣ ወጭንና ጉልበትን ለመቀነስ እያስቻለ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም የሚጠፉ ቅርሶችን ተንከባክቦና ጠብቆ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍና የቅርሶችን የባለቤትነት ጥያቄ ችግርን ለመፍታት ስለሚያስችል ትኩረት መስጠት ይገባል ሲሉ ምክራቸውን ሰንዝረዋል።

ለዚህም በጎንደር ዩንቨርሲቲ 10 የዲጅታል ቤተ መጻህፍትን በማቋቋም 199 ሺህ መጻህፍትን፣ የምርምር ስራዎችንና ሌሎች መዛግብቶችን ወደ ኮምፕዩተር በማስገባት ለተመራማሪዎች፣ መምህራንና ተማሪዎች ክፍት መደረጉን ተናገረዋል።

ይሁን እንጂ ዲጅታል ላይብረሪን በማቋቋም ወጥ የሆነ የአሰራር ስርዓት፣ ፖሊሲ፣በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሃይልና ለዘርፉ ልማት ድጋፍ የሚያደርጉ አካላት አለመኖር ዋና ዋና ችግሮች መሆናቸውን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቤተመጻህፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ የሪከርድና መዛግብት ዳይሬክተር አቶ ሰሎሞን ጠና እንዳሉት በአገራችን ያሉ ክልሎች የራሳቸውን ቤተ መጻህፍትና ቤተ መዛግብት በማቋቋም ትክክለኛ ማንነትን ለትውልድ ማስተላለፍ ይጠበቅባቸዋል።

የሌሎች አገራት ተሞክሮ የሚያሳየውም ክማዕከላዊ መንግስቱ አስቀድሞ ቤተመዛግብት ማደራጀትና መረጃዎችን ማሰባሰብ ያለባቸው ክልላዊ መስተዳድሮች ሲሆኑ በኛ አገር እስከ አሁን ባለው ልምድ ከኦሮምያ ክልል ውጭ ያደራጀ ክልል የለም ብለዋል ።

የአማራ ክልልን ጨምሮ ሌሎች ክልሎች ህብረተሰባዊ መስተጋብርና ጥንታዊ ቅርሶችን ለመጠበቅና ለመጭው ትውልድ ለማስተላለፍ ቤተ መዘክሮች ማቋቋም አለባቸው ብለዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ አዋጅን በሚያሰራ መልኩ በማሻሻል፣ ፖሊሲ በማዘጋጀትና ሌሎች ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ከምሁራንና ተሳታፊዎች የተነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ኤጀንሲው በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።

በአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የባህል ባለሙያ አቶ ቢተው ህሊያ እንዳሉት በአማራ ክልል የሚገኙ ህዝቦችን ባህል፣ ወግ፣ ታሪክና ሌሎችእሴቶች ያካተተ ደረጃውን የጠበቀ የባህል ማዕከል ለማስገንባት ተግባራዊ እንቅስቃሴ እየተካሄደ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በክልል፣ በዞንና ብሄረሰብ አስተዳደር ዞኖችና ወረዳዎች የባህል ማዕከላትን ለማስገተንባት ፍላጎት ቢኖርም ፕላን ተዘጋጅቶ ባለመቅረቡ የሚነሱ ያቄዎችን ለመመለስ እንደተቸገሩ ገልጸዋል።

የተካሄደው የፓናል ውይይትም ለአንድ ሳምንት በባህርዳር ከተማ ሲካሄድ የሰነበተው የንባብ ባህልን የማሳደግ ፕሮግራም አካል መሆኑን ከወጣው መርሃ ግብር መረዳት ተችሏል።

 
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም