በሴቶችና ህጻናት ላይ እየደረሱ ያሉትን ጥቃቶችን ለመከላከል ህብረተሰብ ድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ተገለፀ

294
ኢዜአ/ ህዳር 16 /2012 በሴቶችና ህጻናት ላይ እየደረሱ ያሉትን ጥቃቶችን ለመከላከል በሚደረግ ጥረት ህብረተሰብ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ የትግራይ ክልል ሴቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አሳሰቡ። የነጭ ሪቫን ቀን ትናንት በክልሉ ደረጃ በመቀሌ ከተማ ተክብሯል። ቀኑን ምክንያት በማድረግ በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ የቢሮው ኃላፊ ዶክተር የትምወርቅ ገብረመስቀል እንዳሉት በክልሉ ሴቶችና ህጻናት ላይ የአስገድዶ መድፈር፣ ትንኩሳ፣ ጠለፋና ሌሎች ጥቃቶች እየደረሱባቸው ነው። ሴቶችና ህጻናት ደህንነታቸው ተጠብቆ በሃገራቸው ልማት ላይ ድርሻቸውን እንዲወጡ ለማስቻል ከማንኛውም ጥቃት ሊጠበቁ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ በተለይ የሃይማኖት መሪዎች፣ መምህራንና መላው ህብረተሰብ በቅንጅት በመስራት ጥቃቱን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ መዎጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡ የነጭ ሪቫን ቀን በሚከበርባቸው ቀናትም የሚመለከታቸው አካላት የሴቶችና ህጻናት ጥቃትን በመከላከል አጋርነታቸውን በተግባር ማረጋገጥ እንደሚገባቸው አሳስበዋል። በትግራይ ሴቶችና ህጻናት ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት ለማስወገድ ሴቶች የኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውንና የውሳኔ ሰጭነት አቅማቸውን ማሳደግ እንደሚገባ የገለፁት ደግሞ በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማእረግ የትግራይ ክልል የንግድ፣ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አብርሃም ተከስተ ናቸው። የሴቶችን ሁለንተናዊ አቅም ለማሳደግም  የክልሉ መንግስት ስትራቴጂካዊ እቅድ ነድፎ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል። ጥቃት በሚፈጽሙ አካላትም በህግ ፊት እንዲጠየቁና ጠበቅ ያለ እርምጃ እንዲወሰድባቸው እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡ የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ባካሄደው ጥናት ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ በትግራይ ክልል ውስጥ ከ700 በላይ የሚሆኑ ሴት ህጻናት ያለ እድሜ ጋብቻ የፈፀሙ ሲሆን 480 በሚሆኑት ላይ ደግሞ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል እንደተፈጸመባቸው ማረጋገጡን በውይይቱ ላይ ተገልጿል። ትናንት በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ ተሳታፊ የነበሩ በትግራይ ምእራባዊ ዞን የሰቲት ሑመራ ከተማ ነዋሪ ሓጂ ሰይድ ኢብራሂም እንዳሉት፣ ሴቶች ልዩ ክብርና ጥበቃ ሊደረግላት ይገባል። ''ከሚደርስባት ጥቃት ለመከላከልም ሁላችንም ከጎናቸው ልንቆም ይገባል'' ብለዋል፡፡ ‘’ለህዝቦች እኩልነት፣ነጻነትና አንድነት ሲሉ ከወንድ እኩል ውድ ህይወታቸውን ለከፈሉ የትግራይ ክልል ሴቶች ልዩ ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል’’ ያሉት ደግሞ የመቀሌ ከተማ ነዋሪ አቶ ስዩም ኪዳነ ናቸው። ወይዘሮ አጀብነሽ አብርሃ የተባሉት በትግራይ ምእራባዊ ዞን የወልቃይት ወረዳ ነዋሪ በበኩላቸው፣ በሴቶችና ህጻናት ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት ለመከላከል የፍትህ አካላት በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል፡፡ ትናንት በመቀሌ ከተማ በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ ከአንድ ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና  የስራ ኃላፊዎች ተገኝቷል።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም