ሆስፒታሉ ከህንድ ከሚመጡ የህክምና ባለሙያዎች ጋር በመተባበር የነጻ ህክምና አገልግሎት መስጠት ሊጀምር ነው

80
ኢዜአ/ ህዳር 16 /2012 የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከህንድ አገር ከሚመጡ ስፔሻሊስት ዶክተሮች ጋር በመተባበር ህክምናን በነጻ ሊሰጥ ነው። የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር  አቶ አሸናፊ አምብሬ ለኢዜአ  እንደገለጹት ሆስፒታል ከህንድ አገር ከሚመጡ ስፔሻሊስት ዶክተሮችጋር በመተባበር የዓይን፣ የጥርስ፣ የሆድ ዕቃ፣ የፊንጢጣ፣ የወንድ የዘር ፍሬ ከረጢትና የአንጀት መውረድ ቀዶ ህክምና  ለመስጠት አቅዷል። ህክምናው የሚሰጠው ከህዳር 19 እስከ  21 ቀን ድረስ የሚቆይ የነጻ  የህክምና አገልግሎት ሲሆን ለዚህም  ዝግጅት ማጠናቀቁን  ገልጸዋል። ህክምናውን ለመጀመርም ታካሚዎችን የመለየት ምርመራ ከሰኞ ህዳር 15 ቀን 2012ዓ.ም ጀምሮ የሚካሄድ ሲሆን ይኸ ህሙማንን የመለየት ተግባርም በመድሃኒት ታክመው መዳን የሚችሉትንና ቀዶ ህክምና የሚያስፈልጋቸውን ለመለየት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል። በመሆኑም እነዚህ የጤና እክል ያሉባቸው ታካሚዎች ከህዳር 15 ቀን 2012ዓ.ም ጀምሮ በሆስፒታሉ ተገኝተው መመዝገብ እንድሚችሉም ተናግረዋል። ይህ የህክምና አገልግሎት በቀጣይም  በዘመቻ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸው፤ ከአሁን ቀደምም በሆስፒታሉ የፊትና የአፍ ውስጥ ቀዶ ህክምናዎች እንዲሁም የዓይንና የጥርስ ህክምናዎች በነጻ ሲሰጡ እንደነበር  አክለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም