ሀገሪቱ የምታደርገውን የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ በቴክኖሊጂ ለመደገፍ የሚያስችል ተግባር ጀምራለች

74
ኢዜአ ህዳር 16/2012 የኢትዮጵያ መንግስት በአገሪቱ አጠቃላይ የምጣኔ ኃብት ስርዓት ላይ ማሻሻያ በማድረግ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ምጣኔ ኃብት (የዲጂታል ኢኮኖሚ) ለመገንባት የሚያስችል ተግባር በማከናወን ላይ መሆኑ ተገለፀ። በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የኤሌክትሮኒክ ግብይት ስርዓትን መዘርጋት አገሪቱ አለም ባፈራቸው ቴክኖሎጂዎች የዳበረ ምጣኔ ኃብት (ዲጂታል ኢኮኖሚ) ለመገንባት የጀመረችውን ግስጋሴ ያፋጥነዋል ተብሏል። የዚሁ እንቅስቃሴ አካል ተደርጎ የሚወሰድና ዓለም አቀፍ የኤሌክትሮኒክ ግብይትን በኢትዮጵያ ማስጀመር የሚያስችል ስምምነት በትላንትናው እለት በኢትዮጵያና በቻይናው አሊባባ ኩባንያ መካከል ተፈርሟል። በስምምነቱ መሰረት በኢትዮጵያ የሚገኙ አነስተኛና መካካለኛ ኢንተርፕረይዞች ቻይናን ጨምሮ ድንበር ተሻጋሪ ግብይቶችን ሲፈጽሙ በቴክኖሎጂ የታገዘ የሎጂስትክ አገልግሎት ያገኛሉ። የወጣቶችን በቴክኖሎጂ የታገዘ የሥራ ፈጠራ ክህሎት ለማጎልበት የሚያስችል ስልጠናና ድጋፍም የስምምነቱ አካል መሆኑም ተጠቁሟል። በዚሁ ፕሮጀክት ላይ የመከረና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን ጨምሮ የቻይናና ኢትዮጵያ ንግድ ማህበረሰብ አባላት የተሳተፉበት መድረክ ትናንት ህዳር 15 ቀን 2012 ዓም ምሽት ተከናውኗል። "የኢትዮ-አሊባባ ቢዝነስ ፎረም" በሚል የተካሄደውን መድረክ በመተባበር ያዘጋጁት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር፣ የገንዘብ ሚኒስትር፣ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን እና የአሊባባ ኩባንያ ናቸው። በዚሁ ወቅት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር እዮብ ተካልኝ በተለይም ለኢዜአ በሰጡት ቃል አገሪቱ የኢኮኖሚ ማሻሻያ በማድረግ የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት ሥራ ላይ መሆኗን አውስተዋል። መሰረተ ልማት፣ ኤሌክትሮኒክስ ንግድ፣ የቱሪዝም ሴክተር እድገት እና ስራ ፈጠራ ላይ ዲጂታል ምጣኔ ኃብት ለመገንባት እየተሰራ ነው መሆኑንም አንስተዋል። በአገሪቱ ዓለም አቀፍ የኤሌክትሮኒክ ግብይትን መጀመር አገሪቱ ውስጥ ያሉ ምርቶችን በተቀናጀና በተፋጠነ መንገድ ወደዓለም ለመሸጥ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል። የአሊባባ ኩባንያ በኢትዮጵያ ስራ መጀመር በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አካላት በአገሪቱ የሚከናወነውን የኤሌክትሮኒክስ የግብይት ስርዓት የሚጨፈልቅ አይደለም ያሉት ዶክተር ኢዮብ ይልቁንም ኩባንያዎቹ ሥራቸውን በተሻለ መንገድ እንዲሰሩ ተጨማሪ ጉልበት እንደሚሆናቸው አመላክተዋል። ዓለም አቀፍ የኤሌክትሮኒክ ግብይት በኢትዮጵያ ቱሪዝምን፣ የውጪ ንግድን እና የስራ ፈጠራን የበለጠ እንዲቀላጠፍ በማድረግ አገሪቱ የበለጠ ተጠቃሚ እንድትሆን እንደሚያደርግም ተናግረዋል። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌታሁን መኩሪያ በበኩላቸው፣ የአሊባባ ወደኢትዮጵያ መምጣት የአገሪቱን የቴክኖሎጂ መጠቀም ከፍ ከማድረግ ባሻገር ጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶችን ያበረታታል ብለዋል። አሊባባ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት በዓለም አቀፍ የኤሌክትሮኒክ ግብይት፣ ቱሪዝም ቢዝነስ፣ ቴክኖሎጂ፣ የዲጂታል ኢኮኖሚ ስልጠናዎች ላይ ትልቅ እድል እንደሚፈጥር ነው የተናገሩት። የኢንቨስትመንት ኮሚሽነሩ አቶ አበበ አበባየሁ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ እሴት ተጨምሮባቸው የሚመረቱ ምርቶች በኤሌክትሮኒክ ግብይት ስርዓት በመሸጥ ካለአስፈላጊ ውጪ ያድናል ብለዋል። ዓለም አቀፍ የኤሌክትሮኒክ ግብይቱን ወደ ኢትዮጵያ ማምጣት የወጪ ንግድ፣ ቱሪዝምን አና ሌሎች የኢኮኖሚ  ዘርፎችን ለማሳደግ የሚጠቅም ዘመናዊ የዲጂታል ኢኮኖሚ ማዕቀፍ መሆኑንም ነው ያስረዱት። የአሊባባ ግሩፕ ምክትል ፕሬዚዳንት ብሪያን ኤ ዋንግ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለዲጂታል ቴክኖሎጂ የሰጠችው ትኩረት፤ ዓለም አቀፍ የኤሌክትሮኒክ ግብይትን በአገሪቱ ለማስጀመር ማስቻሉን ገልፀዋል። አሊባባ ኩባንያ በኤሌክትሮኒክ ግብይት፣ በአቅም ግንባታ፣ በኤክስፖርት መጋዘን ግንባታ፣ ለአገር ውስጥ ስራ ፈጣሪዎች በዲጂታል ኢኮኖሚ ሥልጠና እና ግንዛቤ መፍጠር ዙሪያዎች ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚሰራ ተናግረዋል። ለም አቀፍ የኤሌክትሮኒክስ ግብይት (eWTp) በአሊባባ ሀሳብ አመንጪነት በአውሮፓዊያን 2016 የተቋቋመ የኢንተርኔት ቀጥታ ግብይት ስርዓት ሲሆን ዓላማውም አነስተኛና መካከለኛ ሥራ ፈጣሪዎች ምርቶቻቸውን ለገበያ በማቅረብ ሂደት የሚያጋጥማቸውን ችግር መፍታትና ምጣኔ ኃብታዊ እድገትን ማፋጠን ነው። የአሊባባ ኩባንያ ከ20 ዓመት በፊት ከዜሮ ተነስቶ አሁን ላይ ከአንድ ትሪሊየን ዶላር በላይ እያገበያየ ያለ ኩባንያ ነው። በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ሀብት በማካበትም ከ40 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ እድል የፈጠረ የቻይና ኩባንያ ነው።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም