ማህበራዊ ሚዲያን ለበጎ አላማ

231
በሀብታሙ አክሊሉ (ኢዜአ) ማህበራዊ ሚዲያ ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ስርአትን ለመገንባት ከሚያስችሉ እሴቶች ውስጥ አንዱ የሆነውን ሃሳብን በነፃነት የማንሸራሸር ዕድልን ያመቻቻል። ባለን የማህበራዊ ሚዲያ አካውንት ካለንበት ቦታ ሆነን የትኛውንም ሃሳብ የመግለፅ ነጸነትን ያጎናፅፈናል። ማንኛውንም አይነት ይዘት ያላቸው መረጃዎችን ለበርካታ ተከታዮቻችን በተመጠነ ዋጋና በፈጠነ ለማስተላለፍም የማህበራዊ ሚዲያ ሚና የጎላ ነው። ለዚህም ነው እንግዲህ ማህበራዊ ሚዲያ ሃሳብን በነፃነት በማንሸራሸር ለዲሞክራሲ ስርአት መገንባት ሰፊ ሚናን ይጫወታል የሚባለው። ማህበራዊ ሚዲያን ለበጎ አላማ ከተጠቀምንበት ፈርጀ ብዙ ችግሮችን በመቅረፍ የማህበረሰብ ለማህበረሰብ ግንኙነቶችን ልናጠናክርበት እንችላለን። በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቻችን ውስጥ የሚገጥሙንን ፈታኝ ሁኔታዎች ለመሻገር የሚያስችሉ መላዎችን ማህበራዊ ሚዲያ ሊጠቁመን ይችላል። እልቆ መሳፍርት የሌላቸውን ማህበራዊ ጉዳዮች በማህበራዊ ሚዲያ አማካይነት ለማከወን እንችላለን። ማህበራዊ ሚዲያን ሃዘን የገጠማቸውን ለማፅናናት፤ በደስታ ውስጥ የሚገኙትን ደስታቸውን ለመጋራት፣ የታመሙትን ለማበርታት ብሎም ሌሎችን በማስተባበር ከህመማቸው እንዲያገግሙ ለማድረግ፣ የተቸገሩትን ለመርዳት ወዘተ ጥቅም ላይ ልናውለው እንችላለን። አሁንም በርካቶች እያደረጉት የሚገኘው ይህንኑ ነው። ሰዎች የማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ቢዝነሶቻቸውን ያሳድጉበታል፤ የተሻሉ የስራ ዕድሎችን ያመቻቹበታል። ከተለያዩ ደንበኞቻቸው ጋር ይተዋወቁበታል፤ አልፎ ተርፎም በዕለታዊ የቢዝነስ እንቅስቃሴዎቻቸው ዙሪያ ይመክሩበታል፤ ይዘክሩበታል። በማህበራዊ ሚዲያ አማካይነት በሚፈጠሩ የቢዝነስ አማራጮች ማደግ ሳቢያም ዜጎች ዘርፈ ብዙ የስራ ዕድሎች ይፈጠርላቸዋል። እግረ መንገዱንም መንግስት የስራ አጥ ቁጥሩን ከመቀነስ ባሻገር ምጣኔ ሃብቱንም በጠንካራ መሰረት ላይ ሊገነባ ይችላል። እነዚህ ቀደም ብለን የጠቃቀስናቸው አብነቶች ወደ ተቋማት ሲመጡም ጠቀሜታቸው እምብዛም የተለየ አይደለም። በተለይ የመንግስት ተቋማት የማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም አገልግሎት አሰጣጣቸውን በማሳለጥ በህዝብ የሚቀርብባቸውን ቅሬታ ለመቀነስ ሊጠቀሙበት ይችላሉ።   የመንግስት ተቋማት ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም የአገልግሎት አሰጣጣቸውን ሁኔታ የተመለከቱ መረጃዎችን በመሰብሰብ ግብረ መልስ ሊያጠናቅሩበት፣ የተገልገያቸውን አመለካከት በአዎንታዊ መሰረት ላይ ለመገንባት የሚያስችል ግንዛቤን ለመፍጠር፣ ውስን በሆነ ሃብት በርካታ ተግባራትን ለማከናወን ሰራተኞቻቸውን ሊያነቃቁበት፣ በአገልግሎት አሰጣጣቸው ዙሪያ የሚሰጡ አስተያየቶችን በመሰብሰብ ለመተንተን እንዲሁም አገልግሎት አሰጣጣቸውን የደንበኞቻቸውን ቅሬታ መሰረት አድርገው ይፈቱበታል። ተቋማት በቀውስ ጊዜ ላይ በሚገኙበት ወቅትም የተለያዩ ሃሳቦችን በማንሸራሸር ከቀውስ ውስጥ ለመውጣት ማህበራዊ ሚዲያ አይነተኛ ሚና አለው። ይህንኑ ጉዳይ ከግንዛቤ አስገብተው ይመስላል በአሁኑ ወቀት አብዛኞቹ የመንግስት ተቋማት የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች እየሆኑ ነው፤ ምንም እንኳ ተቋማቱ ማህበራዊ ሚዲያን ውጤታማ በሆነ መልኩ ስለመጠቀማቸው ጥናት ማድረግን የሚጠይቅ ቢሆንም። የተቋማቱን ለጊዜው እዚህ ላይ ገታ እናድርገውና ለመሆኑ በእነዚህ የመንግስት ተቋማት በሃላፊነት የተቀመጡ ሰዎች ማህበራዊ ሚዲያን እንዴት እና በምን መልኩ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ የሚለውን ጉዳይ በአጭሩም ቢሆን ለማንሳት ወደድኩ። በመንግስት ተቋማት ውስጥ በሃላፊነት የሚሰሩ ሰዎች የማህበራዊ ሚዲያን እንዴት ይጠቀሙበታል ብለን ስንጠይቅ ሃላፊነታቸው ከሚሰጣቸው መብትና ካለባቸው ግዴታ አንፃር ሊፈተሹ የሚገባቸው ጉዳዮችን ታሳቢ በማድረግ ነው። አንድ የመንግስት ሃላፊ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚለጥፈው መልክዕክት እንደ እኔ ተራ የሆነ ግለሰብ ከሚለጥፈው በብዙ እጥፍ ለተጠያቂነት የተጋለጠ እንደሆነ ይታመናል። ምክንያቱም አንድ በመንግስት ሃላፊነት ላይ የተቀመጠ ግለሰብ ማህበራዊ ሚዲያን አስመልክቶ የሚለጥፋቸው መረጃዎች ለተለያዩ የሴራ ትንታኔዎች ይጋለጣሉና። ይህም ሲባል ቁጥራቸው ትንሽ የማይባል በሃላፊነት ላይ የሚገኙ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም የራሳቸውንም ሆነ የሚመሩትን ተቋም በአዎንታዊ መልኩ ገንብተውት ተመልክተናል፤ እየገነቡትም ይገኛሉ። የማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ሃላፊዎቹ ተቋማቸው እየሰጠ የሚገኘውን አገልግሎት ከመግለፅ ባሻገር ተቋሙ ከየት ተነስቶ የት ሊደርስ እንዳሰበ የሚያስገነዝቡ መረጃዎችን በማሰራጨት ለተገልጋዮቻቸው ግልፅነትን ያዘሉ መልዕክቶችን ሲያስተላልፉባቸው ታዝበናል። ከዚህም በዘለለ መንግስትን ዕለታዊ ሁነቶቹን ለህዝብ በቀላሉ እና በተፋጠነ መልኩ ተደራሽ እያደረገበት ይገኛል። በተቃራኒው አንዳንድ ተቋማት ማህበራዊ ሚዲያዎቻቸውንም ሆነ ሌሎች ድረ ገፆቻቸውን ዞር ብለው ያለማየት ሁኔታም በዚህ ወቅት እንኳ የምንታዘበው ነው። ተቋማቱ በርካታ ተገልጋዮችን እያስተናገዱ እንኳን የማህበራዊ ሚዲያ አካውንት የሌላቸው ከመሆኑም በላይ ያላቸው እንኳን በአዳዲስ መረጃዎች ለደንበኞቻቸው ተደራሽ ሲሆኑ አይታይም። ስለሆነም ተቋማቱ ከጊዜው ጋር ሊራመድ የሚችል ዘመናዊ አሰራር ከመዘርጋት ባልተናነሰ ከደንበኞች ጋር ግንኙነት የሚፈጥሩባቸውን ዘዴዎች ሊያዘምኑት እንደሚገባ አስረጂ አያስፈልግም። የሚናቅ መረጃ በሌለበት በዚህ ዘመን ተቋማቱ እያንዳንዷን መረጃ በኪሱ ይዞ ከሚንቀሳቀስ ዜጋ ጋር ተጓዳኝ የሆነ አደረጃጀትን ሊያዳብሩ ይገባል። እያንዳንዱ ዜጋ ከደህንነት ተቋማት እምብዛም የማይተናነስ መረጃ በሚያገኝበት ዘመን ላይ እንደመገኘታቸው የመንግስት ተቋማት ከቆቅ በላይ ንቁ ሆነው መዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል። ለዚህም የማህበራዊ ሚዲያ ጥቅምን ተረድቶ መንቀሳቀስ ጊዜ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ አይደለም። ማህበራዊ ሚዲያን በአዎንታዊ መንገድ መጠቀም የራስንም የተቋምንም ስም እንዴት ሊገነባው እንደሚችል ከላይ በቀረቡት አስረጂዎች አማካይነት በመጠኑም ቢሆን ለመተንተን ተሞክሯል። የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማችንን ከላይ ስንጠቅስ ከነበረው በተቃራኒው ካደረግነው ግን ውጤቱም ተቃርኖውን ሊይዝ እንደሚችል ወቅታዊውን የሃገራችን ሁኔታ በማየት ለመገንዘብ ይቻላል። ሃሳቡን ከማጠናከር አንፃር ከላይ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚለጥፏቸው መልዕክቶች (ምንም እንኳ አካውንቱ የግላቸው ቢሆንም) የሚኖራቸው አንድምታዎች ከእነርሱ የዘለለ ነው። አንድ የመንግስት የስራ ሃላፊ በማህበራዊ ሚዲያ የግል አካውንቱ ላይ ግጭት ቀስቃሽ መልዕክትን ቢያስተላልፍ ችግሩ ከእሱ አልፎ የሃገር ሰላምን ሊያናጋ የሚችልበት ሁኔታ ፈጣን ነው። መሰል ሁኔታዎችን ከቅርብ አመታት ወዲህ እያየንና መዘዛቸውንም አብረን እየተጋፈጥነው እንገኛለን። ስሜታዊ የሆኑ ሃሳቦች በአንድ ባለስልጣን አይደለም በተራ ግለሰቦችም በማህበራዊ መዲያ ሲቀነቀኑ ሊያመጡ የሚችሉትን ሃገራዊ የሰላም መደፍረስ እየተመለከትን እንገኛለን። የተሰጠውን የህዝብ አደራ የዘነጋ የስራ ሃላፊ ማህበራዊ ሚዲያን አላስፈላጊ የሆኑ መልክዕቶችን እንዲተላለፉበት በማድረግ ያልተፈለጉ መስዋዕትነቶችን ሊያስከፍል እንደሚችል የአደባባይ ምስጢር ነው። በመንግስት ትልቅ ሃላፊነት ላይ የተቀመጡ የስራ ሃላፊዎች የማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ስድብ እየተለዋወጡ ‘አንተ አንቺ’ ሲባባሉ ማየት እጅግ አሰፋሪ ከመሆኑም በላይ እየተለመደ መጥቶ ለበርካቶች ህይወት መጥፋት ምክንያት ሲሆን በቅርብ አመታት ውስጥ ተመልክተናል። ህዝብ እነሱን እንዲወክል ሰፊ ቦታ ሰጥቷቸው ሳለ የመጡበትን ጎሳ በመወከል ከእኔ አይደለም በሚሉት ወገን ላይ ያልተገባ ዘለፋን መወርወሩ ስራዬ ብለው የያዙ ሃላፊዎችን አይታ ሃገር አዝናለች፤ አንገቷንም ደፍታለች። መሰል የስራ ሃላፊዎች ሰፊውን ህዝብ አይደለም ራሳቸውን ለመወከል የሚያስችላቸው ደረጃ ላይ እንደማይገኙ ተግበራቸው ያሳብቅባቸዋል። የትኛውም የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ማህበራዊ ሚዲያን ለጥላቻ ማስፋፊያ ሲጠቀምበት ሲታይ ያሳምማል፤ ይህ ሁኔታ ደግሞ በመንግስት የስራ ሃላፊዎች እየተፈፀመ ሲታይ ደግሞ ሃገር በጠና ህመም ውስጥ ለመሆኗ ማሳያ ሊሆን ይችላል። ምን ይደረግ በመጀመሪያ ደረጃ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ለተራው ዜጋም ሆነ የመንግስት ኃላፊነት ላይ ለሉት ሰዎች የሚሰራ ህግና የስነ ምግባር ደንብ ሊኖረው ይገባል። በተለይም ደግሞ መንግስት ኃላፊነታቸውን ዘንግተው ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶችን በሚያሰራጩ የስራ ሃላፊዎች ላይ ፈጣን እና ጠንከር ያለ እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባ ነጋሪ አያስፈልገውም። ምክንያቱም የመንግስት የመጀመሪያው ተግባር የዜጎቹን ደህንነት መጠበቅ ነውና።  ከዚህ አንፃር ሃላፊዎቹ በህዝብ የተሰጣቸው አደራ ሌላው ተራ ግለሰብ እንደሚያደርገው ነፃነትን ሊሰጥ አይችልምና በጥንቃቄ እንዲሆን መመካከሩ አይከፋም። የስራ ሃላፊዎች ያልተገባ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ከሃገር ደህንነት ጋር የተያያዙ ምስጢራዊ መረጃዎች እንዲያፈተልኩ ምክንያት ይሆናልና በዚህ ረገድም ጠለቅ ያለ ግንዛቤን መንግስት ሊፈጥር ይገባል። በተጨማሪም መንግስት አሁን የጀመረውን የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም (የህዝቡን ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ሳይነካ) ወደ ህጋዊ ማህቀፍ የመውሰድ ሂደት በማፋጠን ማህበራዊ ሚዲያዎች ከጥላቻ መስበኪያነት በጎ በጎ ጉዳዮችን ለማሳለጥ እንዲውሉ ማድረግ ይጠበቅበታል እንላለን።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም