ጽህፈት ቤቱ ኤች አይ ቪ ኤድስን ቀድሞ በመከላከል ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል - ተወካዮች ምክር ቤት

121
ኢዜአ ህዳር 15 /2012ዓ.ም የፌደራል ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት ኤች አይ ቪ ኤድስን ቀድሞ መከላከል ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ። የምክር ቤቱ የሴቶች፣ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የጽህፈት ቤቱን የሩብ ዓመት አፈጻጸም ገምግሟል። በዚሁ ወቅት እንደተገለጸው፤ የበሽታው የስርጭት አማካይ መጠን በአገር አቀፍ ደረጃ 0 ነጥብ 9 ሲሆን ስርጭቱ የከተማው ከገጠር በ7 እጥፍ ይበልጣል። በከተማ ስርጭቱ 3 በመቶ ሲሆን በማረሚያ ቤቶች፣ በሴተኛ አዳሪዎችና የረጅም ርቀት መኪና አሽከርካሪዎች ላይ መጠኑ ከፍ ያለ ነው። በተለይም ስርጭቱ ሴቶችና ህጻናት ላይ ጎልቶ እንደሚታይ የተገለጸ ሲሆን፤  23 በመቶ በየዓመቱ ከሚያዙት ሰዎች ውስጥ 11 ሺህ ያህሉ ሲሞቱ ከነዚሁ ውስጥ 58 በመቶዎቹ ሴቶች ናቸውም ተብሏል። የምክር ቤቱ አባላት ኤች አይ ቪን የመከላከሉና የመቆጣጠሩ ሥራ ተቀዛቅዟል በሚል ግምገማ አድርገዋል። የጸረ ኤች አይ ቪ መድሃኒት አቅርቦት፣የግንዛቤና ንቅናቄ ሥራውም የየአካባቢውን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ ነው የሚል ሀሳብ አንስተዋል። ''በተለይም ጽህፈት ቤቱ ለጋሾች ላይ ከመንጠልጠል ይልቅ በራስ አቅም የሚሰራበትን መንገድ ሊያጤን ይገባል'' ያሉት አባላቱ ቅንጅታዊ አሰራሮችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚኖርበትም አሳስበዋል። ክልሎችም የበሽታን ስርጭትና አሳሳቢነት ከቁብ እየቆጠሩት አይደለም፤ ትኩረት እንዲሰጡበት መስራት እንደሚገባም ነው የምክር ቤቱ አባላት ያመላከቱት። የጽህፈት ቤቱ የእቅድ፣ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክተር አቶ ነጻነት ሀኒቆ በሰጡት ማብራሪያ ግንዛቤ ለማስጨበት ከተለያዩ ቴሌቪዥን፣ሬድዮና ጋዜጦች ጋር በመተባበር ትምህርት አዘል መልዕክቶች እየተላለፉ ነው ብለዋል። በትግራይና አማራ ክልል ለተጠቂዎች የሚሰጡ ማህበረሰብ አቀፍ ድጋፍና ክብካቤ ተሞክሮም ወደ ሌሎች ክልሎች እንዲሰፋ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል። እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ከ476 ሺህ በላይ ተጠቂዎች የጸረ ኤች አይ ቪ መድሃኒት እየወሰዱ ነው፤ 70 ሺህ 800 የሚሆኑት ደግሞ የምግብ ድጋፍ አግኝተዋል። በበሽታው የተያዙ ዜጎች እራሳቸውን እንዲችሉም የገቢ ማስገኛ ስልጠና መሰጠቱን ጠቁመው መነሻ ካፒታልም መሰጠቱን ተናግረዋል። ከመድሃኒት ግዥ ስርአቶች ጋር ያሉ ችግሮች፣መዘግየቶች እንዲሁም በአንዳንድ ክልሎች ምንም አይነት እንቅስቃሴ ያለማድረግና ትኩረት ያለመስጠት ችግር ግን አሁንም ፈተና መሆኑን ነው አቶ ነጻነት ያብራሩት። ጽህፈት ቤቱ በራሱ አቅም ለመንቀሳቀስ ሀብት መሰባሰቢያ ስትራቴጂ እየተቀረጸ ነው፤ ስትራቴጂው እንዳለቀ ለሚመለከተው አካል ቀርቦ ከጸደቀ በኋላ ሥራ ላይ እንደሚውል የተናገሩት ደግሞ የጽህፈት ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አቶ አብርሃም ገብረመድህን ናቸው። በአገር አቀፍ ደረጃ የኤች አይ ቪ ኤድስ ምክር ቤት መቋቋሙን ያስታወሱት ምክትል ዳይሬክተሩ ምክር ቤቱ በክልሎችም እንዲስፋፋ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። ለአብነትም በድሬዳዋ፣ ሱማሌ፣ ትግራይና አፋር መቋቋሙን ገልጸው በቀጣይም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ጋምቤላ፣ አማራና ኦሮሚያ ክልሎች በተመሳሳይ እንደሚቋቋሙ ተናግረዋል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም