ህብረተሰቡ የተከላቸውን ችግኞች የመንከባከብ ተሳትፎው ሊጠናከር ይገባል ... አቶ ኡሞድ ኡጁሉ

85
ኢዜአ ህዳር 15/2012 ህብረተሰቡ ባለፈው ክረምት ችግኞ በመትክል ያሳየውን ተነሳሽነትና ተሳትፎ በመንከባከብ ረገድም ሊያጠናክር እንደሚገባ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አሳሰቡ። የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ዛሬ  የአራንጓዴ አሻራ ቀን በማስመልከት በጋምቤላ ከተማ ዙሪያ የተተከሉ ችግኞችን ዛሬ ተንከባክበዋል። በዚህ ወቅት ርዕሰ መስተዳድሩ እንደገለጹት ባለፈው ክረምት እንደ ሀገር የተነደፈውን የአረንጓዴ ልማት አሻራ  በክልሉም  እውን ለማደረግ  የህዝብ ነቅናቄ በመፍጠር  ከእቅድ በላይ ማሳካት ተችሏል። በቀጣይም የህዝብ ንቅናቄ በመፍጠር በክረምቱ የተተከሉ ችግኞች በበጋው ወራት ጉዳት እንይደረስባቸው የክትትልና እንክብካቤ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። ችግኞች መትክል ብቻ ግብ ሰለማይሆን የተተከሉትን በመንከባከብ ጭምር ህዝቡ ተሳትፎውን ሊያጠናከር እንደሚገባም አሳስበዋል። በዕለቱ በክልሉ ከፍተኛ ስራ ኃፊዎች የተካሄደው የችግኝ እንክብካቤ አመራሩ በአረንጓዴ አሻራ ቀን የተከላቸውን ችግኞች ለመከባከብ በገባውን ቃል መሰረት እንደሆነም አመልክተዋል የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሎው ኡቡፕ በበኩላቸው በክልሉ ባለፈው ክረምት የተተከሉ ችግኞች በበጋው ወራት ጉዳት እንዳይደረስባቸው ከደን፣ ከአካባቢና ከአየር ንብረት ቢሮ ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። ዛሬ በክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች የተጀመረው የተተከሉ ችግኞችን የመንከባከቡ ስራ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ባካተተ መልኩ ለማከናውን የንቅናቄ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውንም አመልክተዋል። ኃላፊው እንዳሉት በተጨማሪ በከተማ ፓርኮች የተተከሉ ችግኞችን የሚከባበከቡ ወጣቶች በቋሚነት ተመድበው እየሰሩ ናቸው። በጋምቤላ ከተማ ዙሪያ የተተከሉ ችግኞችን ሲንከባከቡ ከነበሩት መካከል ወጣት በቀለ ባንቲ በሰጠው አስተያየት ችግኞችን በመንከባከብ የስራ እድል እንደተፈጠረለት ገልጿል። በአካካባቢ ልማትና ጥበቃም የዜግነት ግዴታው ጭምር እየተወጣ መሆኑን ተናግሯል። በጋምቤላ ክልል በአረንጋዴ አሻራ ቀን የተተከሉትን ጭምሮ ከ4 ሚሊዮን 700ሺህ  በላይ የዛፍ፣ የፍራፍሬና ሌሎች ችግኞች መተከላቸው ተመልክቷል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም