በደብረ ማርቆስ ከተማ በንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ላይ የተደረገው ዋጋ ጭማሬ አግባብ አይደለም ሲሉ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ገለፁ

119
ደብረ ማርቆስ ሰኔ 14/2010 በደብረማርቆስ ከተማ ካለው የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እጥረት በተጨማሪ የዋጋ ጭማሬ መደረጉ አግባብ አይደለም ሲሉ የከተማው ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ገለፁ። አራት ብር የነበረው የአንድ ሜትር ኪዩብ ውሃ ወደ ሰባት ብር ከ50 ሳንቲም እንዲያድግ ተደርጓል። በከተማው የቀበሌ 06 ነዋሪ ወይዘሮ እጸገነት ይርዳው ለኢዜአ እንደገለፁት የከተማው የውሃ አቅርቦት ደካማ በመሆኑ ነዋሪውን እያማረረ ነው፡፡ ''ከዚህ ብሶ ደግሞ የዋጋ ጭማሪ መድረጉ ተገቢ አይደለም'' ብለዋል። እሳቸው እንዳሉት ከዚህ በፊት ለውሃ በወር ከ30 እስከ 40 ብር ይከፍሉ እንደነበር አስታውሰው አጠቃቀማቸው ምንም ልዩነት ሳይኖረው አሁን በወር ከ200 ብር በላይ እንዲከፍሉ መጠየቃቸውን ገልፀዋል። አያይዘውም የውሃ ባለሙያዎቹ በየወሩ በትክክል ቆጣሪውን ስለማያነቡ የተደራረበ ሒሳብ በአንዴ በማምጣት ለመክፈልም ሲቸገሩ መቆየታቸው አስታውቀዋል። የቀበሌ 04 ነዋሪ ወይዘሮ ዘውዴ ተቀባው በበኩላቸው የውሃ ተመን መጨመር ካለው የኑሮ ውድነት ጋር ተያይዞ በእለት ከእለት ኑሯቸው ላይ ተጽኖ እንደሚያሳድር ገልፀዋል፡፡ እሳቸው እንዳሉት ከዚህ በፊት ከ10 እስከ 15 ብር ይከፍሉ እንደነበር ጠቁመው፤ አሁን በተደረገው የዋጋ ማሻሻያ ከ60 ብር በላይ እንደከፍል ተደርጓል ሲሉ ቅሬታቸውን ተናግረዋል። ውሃ የሚያገኙት ደግሞ በሳምንት አንዴ በመሆኑ በዚሁ ወቅት በጀሪካን ሦስት ብር ድረስ ገዝተው  እንደሚጠቀሙ ገልፀዋል፡፡ በመሆኑም በከተማው የውሃ አቅርቦት ሳይሻሻል የዋጋ ጭማሪ መደረጉ ከቸርቻሪዎች የሚገዙበትን ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር እንደሚያደርገው ጠቁመዋል። የቀበሌ 05 ነዋሪ አቶ ባየ ዝማሙ በበኩላቸው ''የውሃ ታሪፍ መጨመሩ የተጋነነና የኑሮ ውድነቱን ታሳቢ ያደረገ አይደለም'' ብለዋል። እሳቸው የውሃ ስርጭቱ ከሳምንት በላይ ስለሚቆይ ውሃ ባለበት አካባቢ አካባቢ አንድ ጀሪካን እስከ ከ7 ብር በላይ እንደሚገዙ ገልፀዋል፡፡ በመሆኑም የተደረገው የዋጋ ማስተካከያ አግባብ ባለመሆኑ መንግስት ያለውን ችግር ግምት ውስጥ በማስገባት መፍትሔ እንዲሰጥ ነዋሪዎች ጠይቀዋል። የከተማው ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ ጌታነህ በሰጡት ምላሽ በክልሉ የውሃ አገልግሎት የዋጋ ተመን ከወጣላቸው መካከል ደብረማርቆስ አንዱ ነው ። ''አላማውም በከተማው ያለውን የውሃ እጥረት በዘላቂነት መፍታት የሚያስችል ተጨማሪ ግንባታዎችን እና ነባሩን ፓምፕ ለመቀየር እንዲቻል ማህበረሰቡ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት በማሰብ ነው'' ብለዋል ። በተጨማሪም የውሃ ተቋማቱ ጥገናና መሰል ጉዳዮች  በሚያስፈልገው ወቅት እራሱን በራሱ ማስተዳደር እንዲቻል ታስቦ የዋጋ ጭማሬው መደረጉን አስረድተዋል። የውሃ ተመኑ ከዚህ በፊት ለአንድ ሜትር ኪዩብ 4 ብር ይከፈል እንደነበር አስታውሰው አሁን በተደረገው የዋጋ ማሻሻያ ወደ ሰባት ብር ከ50 ሳንቲም መተመኑን ገልፀዋል። በሚሰበሰበው ገቢም በወረፋ ለማዳረስ የሚደረገውን ጥረት ለማስቀረት የተለያየ የማስፋፊያ ስራ እንደሚከናወን ተናግረዋል፡፡ ''ነገር ግን ማህበረሰቡ የሚያቀርበው ቅሬታ ከዋጋ ጭማሪ ጋር በተያያዘ ብቻ ሳይሆን ቀድመን ባለማሳወቃችን ጭምር በመሆኑ ለዚሁ ይርቅታ እንጠይቃለን'' ብለዋል። በከተማ አስተዳደሩ ከ15 ሺህ 130 በላይ የውሃ ቆጣሪ መኖሩ ተጠቁሟል ።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም