ኢትዮጵያን ከሚያዋስኑ ሀገራት ጋር ያለው ድንበር በውል ተለይቶ እልባት ሊሰጠው ይገባል -- የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

61
ህዳር 15/2012 ኢትዮጵያን ከሚያዋስኑ ሀገራት ጋር ያለው ድንበር በውል ተለይቶ እልባት ሊሰጠው እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ በቀጠናው ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጿል። በህዝብ ምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዛሬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን የ 2012 በጀት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ሪፖርት ገምግሟል። በዚህም በኢትዮጵያና ሱዳን፣ በኢትዮጵያና ኤርትራ እንዲሁም በሌሎች ጎረቤት ሀገራት መካከል  ሲንከባለል የመጣውን የድንበር ውዝግብ እልባት እንዲሰጥባቸው የምክር ቤቱ አባላት ጠይቀዋል። በተለይም ከአማራና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ጋር ከምትዋሰንዋ ሱዳን ጋር ያለው የድንበር ውዝግብ ዓመታትን ያስቆጠረ መሆኑን ይገልጻሉ። ሁለቱ ክልሎች በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች እንደሚነሳው ስሞታ ከሱዳን በኩል በሚሰነዘር ጥቃት የአካባቢው አርሶ አደሮች የጥቃቱ ሰለባ እየሆኑ መሆኑንም የምክር ቤቱ አባላት አንስተዋል። የአካባቢውን ኅብረተሰብ በማሳተፍ ዘላቂ ጉርብትናን መፍጠር በሚቻልበት ሁኔታ ላይም ችግሩን ለመፍታት ሚኒስቴሩ ምን እየሰራ እንደሆነ ማብራሪያ ጠይቀዋል አባላቱ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው በቀጠናው ሌሎች ጉዳዮች ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እንጂ ድንበሩም አልተረሳም ብለዋል። ጉዳዩም የአማራና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ማኅበረሰቦች ብቻ ሳይሆን ሀገራዊ ጉዳይ መሆኑም መታወቅ አለበት ብለዋል። ከኢትዮጵያም ከሱዳንም የሚነሱ ጉዳዮች በመኖራቸውም እነዚህን መረጃዎች በጥንቃቄ መመርመር እንደሚገባም ጠቁመዋል ሚኒስትሩ። በቀጣናው በርካታ ቅድሚያ የሚሰጣቸው የውስጥ ጉዳዮች እንዳሉና እየተሰራባቸው መሆኑንም አንስተዋል። የድንበሩም ጉዳይ የተተወ አለመሆኑን የገለጹት አቶ ገዱ፤ በአሁኑ ወቅት ከሱዳን ጋር ውይይት እየተደረገና ባጠቃላይም ከጉረቤት አገራት ጋር ያለውን ዝርዝር መረጃ የሚሰጥ ካርታ እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል። በተመሳሳይም ከኤርትራ ጋር ያለው የድንበር ጉዳይ ኢትዮጵያ የአልጀርሱን ስምምነትና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ መቀበሏን ተናግረዋል። በወቅቱም ቀጠናው ካሉት ዘርፈ ብዙ ነባራዊ ሁኔታዎች አንፃር ሲታይ ከሱዳን፣ ከኤርትራም ሆነ ከሌሎች ጎረቤት ሀገራት ጋር ያለው የድንበር ጉዳይ ብዙም አንገብጋቢ አለመሆኑን ግን ተናግረዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም