ኢትዮጵያ ስደተኞችን ተቀብላ እያደረገች ላለው ድጋፍ ምስጋና ሊቸራት እንደሚገባ ተጠቆመ

100
ሰኔ14/2010 ኢትዮጵያ ስድተኞችን ተቀብላ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ እየፈጸመች ላለው መልካም ተግባር ከፍተኛ ምስጋና ሊቸራት እንደሚገባ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የሽሬ ቅርንጫፍ አስታወቀ። ዓለም ዓቀፍ የስድተኞች ቀን በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን ከሚገኙ አራቱ የኤርትራዊያን ስድተኞች መጠለያ ካምፖች የመጡ ተወካዮች በተገኙበት ትናንት በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ በድምቀት ተከብሯል። በበዓሉ ላይ የተገኙት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የሽሬ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስተባባሪ ሚስቴር ፋፋ ኦሊቨር አቲድዛህ እንዳሉት ኢትዮጵያ የኤርትራን ስደተኞች ጨምሮ ከተለያዩ አገሮች የሚመጡ ስድተኞችን ተቀብላ በሰላም እንዲኖሩ የጎላ አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ ትገኛለች። መጠለያ ቦታ ከመስጠት ጀምሮ ስድተኞች መሰረታዊ የሆኑ ማህበራዊ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ፣ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ገብተው እንዲማሩና ሌሎች በርካታ እድሎች እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ መፍጠሯም ምስጋና የሚያስችራት ነው። እንደ አስተባባሪው ገለጻ መንግስታዊ ያልሆኑ እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው የስድተኞች ኑሮ እንዲሻሻል የኢትዮጵያ መንግስት እያደረገ ያለው እንቅስቃሴም የጎላ ነው። የስድተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር የሰሜን ኢትዮጵያ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተክኤ ገብረኢየሱስ በበኩላቸው  የዓለም አገራት ስደተኞች ወደ አገራቸው እንዳይገቡ ድንበራቸውን በዘጉበት በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በሯን ከፍታ ስድተኞችን በፀጋ እየተቀበለች ያለች አገር መሆኗን አስረድተዋል። ኢትዮጵያ ኤርትራን ጨምሮ ከተለያዩ አገሮች የመጡ ከ900 ሺህ በላይ ስደተኞችን በተለያዩ ስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ተቀብላ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገች ያለች አገር መሆኗንም ተናግረዋል። የስደተኞች ሕይወት እንዲለወጥም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር  የበኩሏን ድርሻ በመወጣት ላይ መሆኗም ለሌሎች አርአያ እንደሚያደርጋትና ምስጋና እንደሚገባት አመልክተዋል። በዞኑ በማይ አይኒ፣ በሽመልባ፣ በህጻፅና በአዲ ሓሩሽ የሚገኙ ኤርትራዊያን ስድተኞችን በመወከል ንግግር ያደረገው ወጣት ቶፊቅ ኑርሁሴን በበኩሉ "ዴሞክራሲያዊ ባልሆነ አስተዳደር ከምንወዳት አገራችን ብንሰደደም በኢትዮጵያ በተደረገልን ወንድማዊ አቀባበልና እንክብካቤ ሰላማዊ ኑሮ እየመራን እንገኛለን" ብለዋል። ትናንት የተከበረውን ዓለም አቀፍ የስድተኞች ቀንን ምክንያት በማድረግ በዋዜማ በኤርትራ ስድተኞችና በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ የእግር ኳስ ክለብ የወንድማማችነት የእግር ኳስ ጨዋታ ተካሂዷል። ከእዚህ በተጨማሪ በኤርትራዊያን ስድተኞች የተዘጋጁ የእደ ጥበብ ሥራዎች በአውደርዕይ መልክ ቀርበው በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ነዋሪዎች በመጎብኘት ላይ ናቸው።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም