ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለሆቴልና ቱሪዝም ኢንቨስትመንት መስፋፋት የጎላ ሚና ይኖረዋል ተባለ

69
አዲስ አበባ ሰኔ 14/2010 ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለአገሪቱ ሆቴልና ቱሪዝም ኢንቨስትመንት መስፋፋት አዎንታዊ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው የግድቡ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ገለጸ። በኢትዮጵያ የሆቴልና ቱሪዝም ኢንቨስትመንት ዘርፍ መነቃቃት የህዳሴው ግድብ ዓለም ዓቀፍ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆን ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ ሊሆን እንደሚችል ተጠቁሟል። በኦዚ አለም አቀፍ የሆቴል አማካሪዎች ድርጅት ተዘጋጅቶ እስከ ሰኔ 17 ቀን 2010 ዓ.ም የሚቆየው 6ኛው የሆቴልና ቱሪዝም ኢንቨስትመንት ዓውደ ርዕይ ዛሬ በሚሌኒየም አዳራሽ ተጀምሯል። የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ታገል ቀኑብህ በመክፈቻ ስነ ሰርዓቱ ላይ እንዳሉት፤ የግድቡ ግንባታ ሲጠናቀቅ ከሚገኘው ኤሌክትሪክ ኃይል ባለፈ በሚፈጠረው ሰው ሰራሽ ሃይቅ የዓሣ እርባታ፣ የጀልባ ትራንስፖርትና የመዋኛ አገልግሎቶች ይጀመራሉ። አገልግሎቶቹ አካባቢው የቱሪስት መስህብ እንዲሆን በማስቻል ዘርፉን ለማጠናከር እንደሚያግዙ ገልፀዋል። በሀይቁ ዙሪያ የሚኖረው ደን የአየር ንብረት ለውጥን ከመቋቋም በተጨማሪ የጎብኝዎችን ትኩረት የሚስብ ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል። ግንባታው እየተከናወነ ባለበት በአሁኑ ወቅት ግድቡን ከ280 ሺህ በላይ ዜጎች መጎብኘታቸውን የገለጹት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ ሲጠናቀቅ በርከት ያሉ የውጭ ጎብኝዎችን ቀልብ  ይስባል ተብሎ እንደሚታመን ተናግረዋል። ግድቡ በሚገኝበት አካባቢ ያሉ ከተሞች ዘመናዊና ሙሉ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ሆቴሎችን እንዲገነቡ እንደሚያበረታታ የገለፁት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ በአሁኑ ወቅት ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳና ግልገል በለስ ከተሞች ሆቴሎች እየተገነቡ መሆኑን ጠቅሰዋል። 'በቀጣይም የሃይል አቅርቦቱ ሲጨምር ዓለም ዓቀፋዊ ሆቴሎችን መገንባት ያስችላል' ብለዋል። በግዙፍነቱ ከአፍሪካ ቀዳሚ የሚሆነውና 6 ሺህ 450 ሜጋ ዋት ሃይል ያመነጫል ተብሎ የሚጠበቀው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ለሆቴልና ቱሪዝም ዘርፉ ብሎም ለአገራዊ እድገት የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ በመገንዘብ የሆቴል ባለቤቶች፣ ባለሙያዎችና ሌሎችም አካላት ቦንድ በመግዛት በግንባታው ላይ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ጥሪ አቅርበዋል። የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሰግድ ጌታቸው በበኩላቸው ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የቱሪስት መዳረሻዎች ለዓለም ለማስተዋወቅ የሆቴልና ቱሪዝም ኢንቨስትመንት ዓውደ ርዕዩ የጎላ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል። በክልሉ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች መሰማራት ለሚፈልጉ ባለሃብቶች የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃለ ገብተዋል። የኦዚ አለም አቀፍ የሆቴል አማካሪዎች ድርጅት መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ቁምነገር ተከተል ድርጅቱ በአገሪቱ ያለውን የሆቴልና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ክፍተት ለመሙላት እንደሚሰራ ገልጸዋል። በዘርፉ ዓለም አቀፍ የገበያ ትስስር እንዲፈጠር፣ የባህልና የእርስ በርስ ትውውቅ እንዲኖር የሚያበረክተው አስተዋፅኦ የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም