ስደተኛዋ ወፍ - በኢሉአባቦር

131
ምናሴ ያደሳ /ኢዜአ/ በዓለም ላይ ረዥም ርቀት የሚሰደዱ(long distance migrating birds) ተብለው ከሚታወቁት የአዕዋፍ ዝርያዎች መካከል በእንግሊዝኛው አጠራር White stork birds ተብለው የሚጠሩት ይጠቀሳሉ ። እነዚህ የአዕዋፍ ዝርያዎች መገኛቸው በአመዛኙ የደቡባዊና ማዕከላዊ አውሮፓ አገራት እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ ። ከሌሎች ዝርያዎች በተለየ ትላልቅ ክንፎች ያሏቸው እነዚህ አዕዋፋት በአንድ ግዜ እስከ አንድ ሺህ ማይል መብረር ይችላሉ ። የሰውነታቸው ቀለም በአብዛኛው ነጭ ሲሆን ከክንፎቻቸው ግራና ቀኝ ጥቁር ቀለም አላቸው ። የእግራቸው ርዝመት እስከ 150 ሴንቲ ሜትር ይደርሳል ። ክብደታቸው ደግሞ እስከ አምስት ኪሎግራም ይመዝናል ። እነዚህ ዝርያዎች ከስጋ ተመጋቢ ፍጡራን ረድፍ ይመደባሉ ። በአብዛኛው የሚመገቡት በደን ክልል ውስጥ የሚገኙ ትናንሽ አጥቢ የዱርእንስሳትና ተሳቢ እንስሳትን ነው ። ማንቁርታቸው ከሌሎች አዕዋፋት የበለጠ ረዥምና ጠንካራ በመሆኑ ከወንዝ ውስጥ የአሳ ዝርያዎችን በቀላሉ በማደን ይመገባሉ ። በአሁኑ ወቅት በብዛት በሚገኙባቸው የአውሮፓ አገራት ኢንዱስትሪ እየተስፋፋ በመምጣቱ ምክንያት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደን በብዛት ወደሚገኝባቸው የአፍሪካና ደቡባዊ አሜሪካ አገራት በስፋት እየተሰደዱ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ ። የወፍ ዝርያዎቹ ለኑሮ ወደሚስማማቸው ቦታዎች ሲሰደዱ ፀሐይ ፣ጨረቃና የመሬት ማግኔቲክ ፊልድ እንደሚጠቀሙም መረጃዎች ያመላክታሉ ። የአውሮፓ አገራት ይህንኑ የአዕዋፋቱን እንቅስቃሴ ለመከታተልና በምድር ላይ የሚኖራቸውን ቆይታ ለማወቅ በአዕዋፋቱ እግር በርካታ መረጃዎችን የያዙ ቀለበቶች በማሰር ይለቃሉ ። ይህንን ስራ የሚያከናውኑትም ራሱን የቻለ ተቋም በመክፈትና መረጃዎቹን በዳታ ቤዝ በመመዝገብ ነው ። ከእነዚህ የአዕዋፍ ዝርያዎች መካከል አንዷ ሰሞኑን በኢሉአባቦር ዞን የደን ክልል ውስጥ ተገኝታለች ። በዞኑ ሰሌ ኖኖ ወረዳ ተፈጥሮ ደን ውስጥ የተገኘችው ይህች ወፍ በደን ውስጥ ከወደቀችበት በአርሶ አደሮች ተይዛ ነው ወደ ፖሊስ ጣቢያ የተወሰደችው ። የወረዳው መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ሐላፊ አቶ እንዳለ ታሪኩ እንደተናገሩት ወፏ በቀኝ እግሯ አረንጓዴ ቀለም ያለው የብረት ቀለበት በግራ እግራ ደግሞ ቀለም የሌለው ቀለበት ታስሮባታል ። በባለቀለም ቀለበቱ ላይ T 4542 የሚል መለያ ቁጥር እንዲሁም በሌላኛው ቀለበት ላይ ሆላንድ የሚል ፅሑፍና ሌላ መለያ ቁጥር እንዳለው አቶ እንዳለ ተናግረዋል ። ወፏ በአርሶአደሮች ተይዛ ስትመጣ በአውሬም ይሁን በሰው ጥቃት እንደደረሰባት የሚያሳይ ምልክት አልተገኘም ። ሆኖም ግን ከሰውነት መድከም የተነሳ ምንም እንቅስቃሴ እንደማታደርግ ነው የተናገሩት:: ይህ ደግሞ ረዥም ርቀት እንደተጓዘች ያሳያል ባይ ናቸው ። ከሰውነቷ መድከም የተነሳ የሚሰጣትን ማንኛውን ነገር መመገብ ባለመፈለጓ ከሁለት ቀን ቆይታ በኋላ መሞቷን ነው የተናገሩት ። የደን ሽፋን እየጨመረ መምጣቱንና የወራጅ ወንዞች በብዛት መኖር አካባቢው የስደተኛ አእዋፋት መዳረሻ እንዲሆን አድርጎታል ሲሉ ኃላፊው ግምታቸውን አስቀምጠዋል ። የአብጃታና ሻላ ሀይቆች ብሄራዊ ፓርክ ሃላፊ አቶ ባንኪ ቡደሞ እንደሚሉት ደግሞ በርካታ የአውሮፓና የኤሲያ አእዋፋት ከመስከረም እስከ ህዳር ድረስ ያሉትን ብርዳማ ወራት የሚያሳልፉት በኢትዮጵያ ነው ። ፍላሚንጎና ፔሊካን የመሳሰሉ አእዋፋት የአብጃታ ሀይቅን የሚመገቡበት የሻላ ሀይቅ ደግሞ የሚራቡበት ቦታ አድርገው ይመርጡታል ። የአእዋፋቱ በስደት ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የተፈጥሮ ሀብታችን መጠበቅና መንከባከብ ከቻልን በሰው ልጆች ቀርቶ በእንስሳትም ተመራጭ እንደሚያደርገን ጥሩ ማሳያ ነው ። በኢሉአባቦር ዞን በአለም ቅርስነት ከተመዘገበውና ከ168 ሺህ ሄክታር በላይ ከሚሸፍነው የተፈጥሮ ደን በተጨማሪ በሰሌ ኖኖ ወረዳ ከ250 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሸፍን የተፈጥሮ ደን መኖሩ ለአዕዋፋቱ ወደ አካባቢው መሰደድ ምክንያት መሆኑ ይገመታል ። በዞኑ የያዮ ተፈጥሮ ደን ውስጥም ከደን መጠን መጨመር የተነሳ ሰሞኑን ካለፉት ጊዜያት በተለየ መልኩ እንደ ጎሽ ያሉ የዱር እንስሳት በብዛት መታየት ጀምረዋል ። በኢትዮጵያ በችግኝ ተከላ እየተካሄደ ያለው ውጤታማ ስራ ይህንኑ የሚያጠናክር ነውና በርትተን ልንገፋበት ይገባል መልእክታችን ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም