ሲዳማ ክልል እንዲሆን የሚያስችለውን ድምጽ ማግኘቱን ቦርዱ አስታወቀ

100
ኢዜአ ህዳር 13/2012 በሀዋሳና ሲዳማ ዞን በተካሄደው ህዝበ ውሳኔ ሲዳማ ክልል ሆኖ መደራጀት የሚያስችለውን ድምጽ ማግኘቱን        ብሄራዊ  ምርጫ ቦርድ አስታወቀ ቦርዱ   ማምሻውን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ  እንዳመለከተው ለህዝበ ውሳኔው ድምጽ ለመስጠት  2 ሚሊዮን 280 ሺህ 147 ሰዎች ተመዝግበው ነበር። ከተመዘገበው ውስጥም 99 ነጥብ 8 በመቶ የሚሆነው ድምጽ መስጠቱን ገልጿል። በዚህም ሻፌታን 2 ሚሊዮን 225 ሺህ 249  ጎጆን ደግሞ 33 ሺህ 463 ሰዎች መምረጣቸውን  ቦርዱ አስታውቀዋል። 18 ሺህ 351 የተበላሸና ዋጋ አልባ ድምጽ እንደሆነም ተጠቁሟል። በውጤቱም መሰረት 98 ነጥብ 51 በመቶ የሚሆነው የዞኑ የሀዋሳ  ነዋሪዎች በፈቃዳቸው በሰጡት ውሳኔ  ሲዳማ ክልል ሆኖ መደራጀት የሚያስችለውን ድምጽ እንዳገኘ ቦርዱ ገልጿል። የህዝበ ውሳኔው ሂደት ሰላማዊና ተአማኒ ከመሆኑም በላይ  ከፍተኛ የህዝብ ተሳትፎ የታየበት እንደነበርም ተመልክቷል። ህዝበ ውሳኔ ዜጎች መብታቸውን በሰላማዊ መንገድ ተግባራዊ ያደረጉበትና በሀገሪቱ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ አንድ እርምጃ ነው ብሎ ቦርዱ እንደሚያምን ገልጿል። ቦርዱ እንዳስታወቀው የህዝበ ውሳኔና የቦርዱ አፈጻጸም የተሳካ ነበር። የድምጽ መስጫ ጣቢያዎችን ለመወሰን የሚያስፈልገው የህዝብ ቁጥር የተሟላ መረጃ አለመኖር ፣በተወሰኑ የሀዋሳ ከተማና ገጠር አካባቢዎች ድምጽ መስጫ ጣቢያዎች ውስጥ የማይመለከታቸው ሰዎች መገኘት ቦርዱ በክፍተትነት ጠቁሟል። ከሀዋሳ ከተማና ከዞኑ አስተዳደር በቦርዱ ይፋዊ መግለጫ ከመሰጠቱ በፊት አስቀድሞ የመገመትና የመግለጽ ችግር ታይቷል ብሏል። በአንዳንድ የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች በህግ የተቀመጠን የምርጫ ጣቢያ መክፈቻና መዝጊያ ሰዓት አለመጠበቅም እንዲሁ። የክልሉ የጸጥታ ተቋማት፣ የሀገር መከላከያ ሰራዊትና የፌዴራል ፖሊስ የህዝበ ውሳኔው ሂደት ሰላማዊ እንዲሆን፣  የአካባቢ ጸጥታና ደህንነት በመጠበቅ በቅንጅት ላበረከቱት  አስተዋጽኦ   ቦርዱ  አመስግኗል። በህዝበ ውሳኔው የተሳተፉ   ነዋሪዎች ሰላማዊና ስነስርዓት ባለው ሁኔታ ላበረከቱት ተሳትፎ፣ ህዝበ ውሳኔውን ላስፈጸሙና ላስተባበሩ አካላትም እንዲሁ አመስግኗል። ከሲዳማ ህዝበ ውሳኔ ድምጽ አሰጣጥ ስነስርዓት በቀጣይ ለሚደረገው ሀገራዊ ምርጫ ትልቅ ተሞክሮ የተወሰደበት  መሆኑን የቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም