የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የነበረብንን ብዥታ አጥርቶልናል - የነቀምቴ ከተማ ነዋሪዎች

70
ነቀምቴ ሰኔ 14/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በወቅታዊ ጉዳይ  ላይ የሰጡት ማብራሪያ ብዥታን በማጥራት ሁሉንም ወገን ለልማትና ለአንድነት የሚያነሳሳ መሆኑን አስተያየታቸውን የሰጡ የነቀምቴ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ። በነቀምቴ ከተማ የደርጌ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ ሙሉጌታ ቢራቱ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፓርላማ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች የሰጡት ምላሽና ማብራሪያ ግልጽነት የተላበሰና የህዝብ ወገንተኝነታቸውን ያንጸባረቀ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ማብራሪያው በተለይ በአልጀርሱ ስምምነትና አፈጻጸም ላይ የነበራቸውን ብዥታ ግልጽ አድርጎላቸዋል። በአሁኑ ወቅት አልፎ አልፎ በአገሪቱ አንዳንድ አከባቢዎች የሚታየው የብሔር ግጭት ከብሔረሰቡ የመነጨ ሳይሆን የከሰሩ የፖለቲካ አቀንቃኞች የሸረቡት ሴራ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ በመሆኑም ህዝቡ አንድነቱን በማጠናከር ድርጊቱን ሊያከሽፈው እንደሚገባ የሰጡትን ማብራሪያ እንደሚደግፉት ተናግረዋል። የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ግጭትም ''በአልጀርሱ ስምምነት መሠረት መፈጸም አለበት'' ብለው ያቀረቡት ተቀባይነት ያለውና ለድርድር የሚቀርብ እንዳልሆነ ገልጸዋል። በከተማዋ የ03 ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሽመልስ አምሣሉ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚፈጠር አለመግባባት መፈታት ያለበት በፍቅር፣ በትዕግስትና በመደማመጥ  እንጂ በጥላቻ፣ በእልህና በበቀል መሆን እንደሌለበት መግለጻቸው አስተዋይ መሪ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው። በተለይ ''የብሔር ግጭት ለእልቂት የሚዳርግና ማንም እንደማያተርፍ ይልቁንም አገሪቱን ለጥፋት የሚዳርግ መሆኑን ሁሉም ወገን አውቆ ለሰላም ቅድሚያ እንዲሰጥ ያቀረቡት ጥሪ ትክክለኛና የሚያግባባን ነው'' ብለዋል። እንዲሁም በኢትዮ-ኤርትራ፣ በታራሚዎችና አሸባሪ ላይ የሰጡት ገለፃና ማብራሪያ እንዳደሰታቸውና እሳቸውም ለተግባራዊነቱ ከጎናቸው እንደሚቆሙ አረጋግጠዋል፡፡ በኦሮሚያ ፍትህ ቢሮ የምዕራብ ኦሮሚያ ችሎት አስተባባሪ ዐቃቤ ሕግ አቶ ገርሞሣ ዱጉማ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአገሪቱ ፓርላማ ያቀረቡት ሪፖርትና የሰጡት ማብራሪያ ወቅታዊና ተገቢነት ያለው ነው። ከዜጎች ሰብአዊ መብት አያያዝ አኳያ የሰጡት ማብራሪያ መንግሥት የዜጎችን ሕገ መንግሥታዊ መብት ለማስጠበቅ ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ገልፀዋል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም