በኢትዮጵያ የጥሎ ማለፍ እግር ኳስ ጨዋታ መከላከያ ድሬዳዋ ከተማን አሸነፈ

59
አዲስ አበባ ሰኔ 14/2010 የክለቦች ጥሎ ማለፍ ውድድር ዛሬ በተደረገ ጨዋታ መከላከያ ድሬዳዋ ከተማን ሶስት ለሁለት አሸንፏል። በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በፍጹም ገብረማርያም ሁለት ጎሎችና በሳሙኤል ታዬ አንድ ግብ መከላከያ አሸንፎ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፏል። ዳኛቸው በቀለ ለድሬዳዋ ከተማ ሁለቱን ግቦች አስቆጥሯል። ቀሪ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የጥሎ ማለፍ ውድድር ጨዋታዎች ዛሬ ሲቀጥሉ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ኢትዮ ኤሌትሪክና መቐለ ከተማ እንዲሁም 11 ከ 30 ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወላይታ ድቻ ጋር ይጫወታሉ። በክልል ከተማ በአርባምንጭ ስታዲየም አርባምንጭ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ ይጫወታሉ። ዛሬ በሃዋሳ ስታዲየም ሃዋሳ ከተማና ሲዳማ ቡና ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ የሃዋሳ ከተማ ክለብ በጊዜያዊነት በመበተኑ ምክንያት ክለቡ ጨዋታው ለሌላ ጊዜ ይራዘምልኝ በሚል ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ ጨዋታው ሌላ ጊዜ ተራዝሟል። ደደቢት ከጥሎ ማለፍ ውድድሩ ራሱን በማግለሉ ምክንያት የጅማ አባጅፋርና የደደቢት የጥሎ ማለፍ ጨዋታ የመካሄድ ጉዳይ እስካሁን አለየለትም። የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የጥሎ ማለፍ ውድድር ሚያዚያ 12 ቀን 2010 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን እስካሁን በተደረጉ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች አርባምንጭ ከተማ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲን፣ ፋሲል ከተማ አዳማ ከተማን እና ኢትዮጵያ ቡና ወልዲያ ከተማን በማሸነፍ ወደ ቀጣይ ዙር ማለፋቸው የሚታወስ ነው።                      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም