የኢህአዴግ ምክር ቤት በፓርቲ ውህደት፣ ፕሮግራምና ህገ ደንብ ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳለፈ

147

ኢዜአ፤ ህዳር 12/2012 የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢህአዴግ/ ምክር ቤት ህዳር 11 እና 12/ 2012 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ በፓርቲ ውህደት፣ በፕሮግራምና ህገ ደንብ ላይ በዝርዝር ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከህዳር 6 እስከ 8 ቀን 2012 ዓ.ም ባደረገው መደበኛ ስብሰባ በፓርቲ ውህደት፣በፕሮግራምና ህገደንብ ላይ ተወያይቶ  በአብላጫ ድምጽ አጽድቆ ለኢህአዴግ ምክር ቤት ማሳፉ ይታወቃል።

ይሄንኑ መነሻ በማድረግ የኢህአዴግ ምክር ቤት ለሁለት ቀናት ባካሄደው ስብሰባ የውህደት ውሳኔ ሃሳቡን፣ የፓርቲውን ፕሮግራምና ህገ ደንብ በዝርዝር ከተመለከተና ካዳበረ በኋላ በሙሉ ድምፅ አጽድቆታል።

ምክርቤቱ የላከው መግለጫ እንደሚያመለክተው ኢህአዴግ ሀገር መምራት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች በርካታ ለውጦችን አስመዝግቧል።

በዚህም የድህነት ምጣኔን በመቀነስ፣ ተከታታይና ፈጣን ዕድገት በማስመዝገብ፣ መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት እና በሌሎች መስኮችም  ስኬቶችን ማስመዝቡን የጠቀሰው መግለጫው  በማህበራዊ ዘርፍ በትምህርትና ጤና አገልግሎት ተደራሽነት መልካም ውጤቶችን ማስመዝገቡን አመልክቷል።

እነዚህ ስኬቶች ቢኖሩም በርካታ ጉድለቶች እንደነበሩ ከዚህ በፊት መገምገሙን በመጥቀስ፤ ኢህአዴግ ጉድለቶቹን ለማረም  ለውጡን መምራት የሚችል፣ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚወከሉበት፣ ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች አንዳችም ልዩነት ሳይደረግባቸው እኩል የሚሳተፉበት፣ እውነተኛ ህብረ ብሔራዊ ፌደራላዊት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ራሱን ፈትሾ የአደረጃጀት፣ የአሰራርና የፕሮግራም ማሻሻያ እያደረገ መሆኑም ተጠቅሷል።

ውህዱ ፓርቲ በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ መሰረት ቀሪ ሂደቶችን በፍጥነት አጠናቆ፤ የቆመላቸውን ዓላማዎች ወደሚያሳካባቸው ተጨባጭ ስራዎች እንዲሸጋገር የሚያስችሉትን አቅጣጫዎችንም ምክር ቤቱ አስቀምጧል።

የምክር ቤቱ ሙሉ መግለጫ 

================

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢህአዴግ/ ምክር ቤት የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢህአዴግ/ ምክር ቤት ከህዳር 11—12 ቀን 2012 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ በፓርቲ ውህደት፣ በፕሮግራምና ህገ ደንብ ላይ በዝርዝር ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡

ኢህአዴግ ሀገር መምራት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች በርካታ ለውጦችን ያስመዘገበ ድርጅት ነው፡፡ የድህነት ምጣኔን በመቀነስ፣ ተከታታይና ፈጣን ዕድገት በማስመዝገብ፣ መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት እና በመሳሰሉት ጉልህ ስኬቶችን ማስመዝቡም ይታወቃል፡፡
 
በማህበራዊ ዘርፍም በትምህርትና ጤና አገልግሎት ተደራሽነት መልካም ውጤቶችን አስመዝግቧል፡፡
 
ይሁን እንጂ በስኬቶቹ ልክ በርካታ ጉድለቶችም የተስተዋሉበት መሆኑን መገምገማችን ይታወሳል፡፡ በተለይም በብሔራዊ ማንነት እና በሀገራዊ አንድነት መካከል ሚዛን ጠብቆ በመሄድ፣ ማህበራዊ ፍትህን በማረጋገጥ፣ እውነተኛ ፌደራላዊ ስርዓት በመገንባት ረገድ ጉድለቶቹ የበዙ ነበሩ፡፡ እንደዚሁም አርብቶ አደሩን የሃገራችንን ክፍል የወከሉ ድርጅቶች “አጋር” በሚል አግላይ አሰራር በሃገራቸው እጣ ፈንታ ላይ ቀጥተኛ ውሳኔ የማይሰጡ የሩቅ ተመልካች እንዲሆኑ ተደርገው ቆይተዋል፡፡
 
በመሆኑም ኢህአዴግ ለውጡን መምራት የሚችል፣ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚወከሉበት፣ ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች አንዳችም ልዩነት ሳይደረግባቸው እኩል የሚሳተፉበት፣ ዘመኑን የዋጀ የነገ ፓርቲ በመሆን እውነተኛ ህብረ ብሔራዊ ፌደራላዊት ኢትዮጵያ እውን እንድትሆን ለማድረግ ራሱን ፈትሾ የአደረጃጀት፣ የአሰራርና የፕሮግራም ማሻሻያ ማድረግ የግድ እንደሚለው በየጊዜው ሲካሄዱ በነበሩ ጉባዔዎችና ድርጅታዊ መድረኮች አቅጣጫ ሲቀመጥ ቆይቷል፡፡
 
በድርጅቱ 11ኛ መደበኛ ጉባዔ የፓርቲ ውህደት አጀንዳ አንኳር ከነበሩት የውይይት አጀንዳዎች ተጠቃሽ ነበር።
 
በጉባዔውም የውህደት ሂደቱ ከሚገባው በላይ የተጓተተ መሆኑን በመገምገም ጥናቱ በፍጥነት ተጠናቆ ወደ ተግባር እንዲገባ ውሳኔ መተላለፉ ይታወሳል። የኢሕአዴግ ምክር ቤትም ጥናቱን እንዲፋጠን በማድረግ ተከታትሎ በማስፈፀም ሃላፊነቱን እንዲወጣ አቅጣጫ ተቀምጦ እንደነበር ይታወቃል።
 
በዚሁ መሰረት ጥናቱ በዘርፉ ልምድና የካበተ እውቀት ባላቸው ምሁራን ተካሂዶ ለየብሄራዊ ድርጅቶች ሊቀ መናብርት፣ ለስራ አስፈፃሚ ኮሚቴና ማዕከላዊ ኮሚቴዎች ቀርቦ ውይይትና አስተያየቶች ተሰጥተውበት እየዳበረ እንዲመጣ ተደርጓል።
 
የኢሕአዴግ ኦዲትና ቁጥጥር ኮሚሽንም ውህደቱ በሁሉም ብሄራዊ ድርጅቶች አባላትና አመራር ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘ እንዲሁም በድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት የተከናወነ ስለመሆኑ በተናጠል ባደረገው ጥናት ያረጋገጠ ሲሆን ይህም ለምክር ቤቱ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
 
በመጨረሻም የኢሕአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከህዳር 06 እስከ 08/ 2012 ዓ.ም ባደረገው መደበኛ ስብሰባ በጥናቱ ላይ ዝርዝር ውይይት አድርጎ በአብላጫ ድምፅ ካፀደቀው በኋላ ውሳኔ እንዲሰጥበት ለምክር ቤቱ አስተላልፏል።
 
ምክር ቤቱም በአሰራሩ መሰረት ለሁለት ቀናት ባካሄደው ውይይት የውህደት ውሳኔ ሃሳቡን፣ የፓርቲውን ፕሮግራምና ህገ ደንብ በዝርዝር ካየና ካዳበረ በኋላ በሙሉ ድምፅ አፅድቆታል።
 
ምክር ቤቱ ውህድ ፓርቲው በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ መሰረት ቀሪ ሂደቶችን በፍጥነት አጠናቆ የቆመላቸውን አላማዎች ወደሚያሳካባቸው ተጨባጭ ስራዎች እንዲሸጋገር የሚያስችሉትን አቅጣጫዎችም አስቀምጧል።
 
የኢህአዴግ ምክር ቤት ይህን ውሳኔ ሲያስተላልፍ እስካሁን የነበረው የኢህአዴግ አደረጃጀትና ፕሮግራም የአቃፊነት ጉድለት የሚታይበት በመሆኑ የባለቤትነት እና የባይተዋርነት አሰላለፍን እንደፈጠረና ይህም ድርጅቱን እና ሀገራችንን ወደ ከፋ ክፍፍል ያመራና ፅንፈኝነትን እየወለደ የሄደ መሆኑን በመገንዘብ አቃፊ የፖለቲካ አቅጣጫን መከተል እንዳለበት በማመን ነው፡፡
 
ለተፈጠረውም ሀገራዊ ችግር መፍትሔው ሁሉም ኢትዮጵያውያን ባለቤት የሆኑበት፤ በሀገራቸው ጉዳይ ራሳቸው የሚወስኑበት ህብረ-ብሔራዊ ፓርቲ መገንባት እና የቡድንና የግለሰብ መብቶች ተጣጥመው የሚሄዱበት የፖለቲካ አውድ መገንባት መሆኑን ምክር ቤቱ አምኖበታል።
 
ውህደቱ በሀገራችን የፖለቲካ ታሪክ አዲስ የአስተሳሰብ ለውጥና እመርታ የሚያመጣ የአንድነት፣ የአብሮነትና የእኩልነት መንፈስን የሚፈጥር ነው። የፓርቲ ውህደቱ ሁሉንም የሚያካትት፣ ተደራሽና ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በማንነቱ ሳይገደብ የሚሳተፍበትን ሁኔታ በመፍጠር ጠንካራ ህብረ ብሄራዊ ፌዴራላዊ ስርዓትን እውን ማድረግ ያስችላል።
 
በተጨማሪም የቡድንና የግል መብትን እንዲሁም ብሄራዊ ማንነትንና ኢትዮጵያዊ አንድነትን በማጣጣም በህገ መንግስታችን ላይ የተቀመጠውን አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመገንባት ራዕይ እውን ለማድረግ የሚያስችል ነው።
 
ውህድ ፓርቲው የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን በማድረግ ግዙፍ አላማ ማእቀፍ ውስጥ የህዝቦች መሰረታዊ ፍላጎቶችን በዘላቂነት ለማሟላት ጥራትና ቀጣይነት ያለው ዕድገት በማስመዝገብና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ያለው ኢኮኖሚ በመገንባት ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ማረጋግጥ፣ የህዝቦችን ድህነት፣ እርዛትና ኋላቀርነትን ቀርፎ ሁሉን አቀፍ ብልጽግና በሃገራችን እውን ሆኖ ለማየት የሚሰራ ፓርቲ ነው።
 
ለዴሞክራሲ ባህል ማበብ አስፈላጊ የሆኑ ባህልና ተቋማት በመገንባት፣ የህዝቦች ነፃነትና እኩልነት ተረጋግጦ፣ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ተከብረውላቸው፣ ህብረ ብሄራዊ አንድነቷ የተረጋገጠባት ፌዴራላዊት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ በፅኑ መሰረት ላይ ማቆም ፓርቲው ከሚታገልላቸው ቁልፍ አጀንዳዎች አንዱ ነው።
 
በማህበራዊ ልማት መስክም መልካም ሀገራዊ እሴቶችና ባህሎችን በማዳበር በስነ ምግባር የታነፀ ትውልድ ማፍራት፣ ለኑሮ ምቹ የሆነ አካባቢን መፍጠር፣ የማህበረሰብ ጤና ተጠብቆ፣ ጥራት ያለው ትምህርት ለሁሉም እንዲዳረስ እና በህዝቦች መካከል አዎንታዊ ሰላም ተፈጥሮ ሁለንተናዊ ብልጽግና እንዲረጋገጥ ይተጋል።
መላው የድርጅታችን አባላትና ደጋፊዎች፤
ድርጅታችን በታሪኩ ያስመዘገባቸውን መልካም ስኬቶች በማስቀጠልና ስህተቶችና ድክመቶችን በማረም የዛሬ ብቻ ሳይሆን የነገው ትውልድ ፓርቲ ይሆን ዘንድ ትግል ስታደርጉ ቆይታችኋል።
 
እነሆ ትግላችሁ ፍሬ አፍርቶ ህብረ ብሄራዊ ቅርፅና አካታችነት መገለጫው የሆነ ሀገራዊ ፓርቲ ለመሆን በቅተናል። በመሆኑም ምክር ቤታችን ለዚህ አዲስ ምዕራፍ በመብቃታችን እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት ይወዳል።
 
ውህደቱ እውነተኛ ዴሞክራሲ፣ ፌዴራላዊና ህብረ-ብሔራዊ ስርዓትን እውን የሚያደርግ፤ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ማንነታቸው በተገቢው መልኩ እውቅና አግኝቶ ሳይሸራረፍ ተግባራዊ የሚሆንበት፤ በመቻቻልና በመከባበር ላይ የተመሠረተች ሀገር ለመገንባት የሚያስችል ስርዓት እውን እንዲሆን እና ሁሉም የሚሳተፍበት የፖለቲካ ምህዳር ለመፍጠር የሚያስችል አደረጃጀት ስለሆነ ለስኬቱም መላ አባላትና ደጋፊዎቻችን ከምንጊዜው በላይ ርብርብ እንድታደርጉ ምክር ቤቱ ጥሪ ያቀርብላችኋል።
 
ለአጋር ድርጅቶች አመራርና አባላት፤ በኢሕአዴግ ጉባዔዎች ጨምሮ በሁሉም የፓርቲ መድረኮች የኢሕአዴግ አባል ፓርቲ እንዳትሆኑ መታገዳችሁ አሳማኝ ምክንያት የሌለው አግላይ አካሄድ መሆኑን በማንሳት ስትታገሉ ቆይታችኋል።
 
ኢሕአዴግም የዚህን ጥያቄ ተገቢነት በማመን ለማስተካከል ከወሰነ አመታት አልፈዋል። ይህን በመፈፀም ረገድ የነበሩ እግር የመጎተት ችግሮች አሁን ተፈትተው ለዚህ ታሪካዊ ቀን በመድረሳችሁ የኢሕአዴግ ምክር ቤት እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት ይወዳል። እንኳን ለዚህ የአጋርነት ታሪክ ምእራፍ የተዘጋበትና አካታች አዲስ የትግል ምዕራፍ የተሸጋገራችሁበት መድረክ አበቃችሁ።
 
ውህድ ፓርቲው ሁላችንም በእኩል የምንታይበትና የምንሳተፍበት አዲስ ፖለቲካዊ ምህዳር በመፍጠር ሀገራችን ያለችበትን ሁኔታ ለመቀየር በሚያደርገው ርብርብ በጋራ ጠንክረን እንድንሰራ ጥሪውን ያቀርብላችኋል።
 
ለተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ፤በሀገራችን ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል መደማመጥ፣ መቻቻል፣ መከባበርና ሚዛናዊ ትብብርና ፉክክር መገለጫው የሆነ የሰለጠነ ፖለቲካ በሀገራችን እውን እንዲሆን፣ የጥላቻና የሴራ ፖለቲካ እንዲቀር መስራት ውህድ ፓርቲው ከሚታገልላቸው አጀንዳዎች ውስጥ ዋነኛው ነው።
 
በመሆኑም እውነተኛ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት እንዲሰፍን በሚያግባቡን ጉዳዮች ላይ በጋራ እየሰራን በማያግባቡን ጉዳዮች ላይ ደግሞ በሰለጠነ፣ ሰላማዊና ህጋዊ በሆነ መንገድ እየተደራደርን ችግሮችን በመፍታት አገራችንን ወደ ብልፅግና ለማሸጋገር በሚደረገው ጥረት የበኩላችሁን ገንቢ ሚና ትጫወቱ ዘንድ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
መላ የሀገራችን ህዝቦች፤ፓርቲያችን አሁን የደረሰበት ደረጃ ሁሉም ኢትዮጵያውያን  በማንነታቸው ሳይገደቡ፤ ቤተኛና ባይተዋር ሳይሆኑ እኩል የሚሳተፉበት የሁሉም መታገያ መድረክ ለመሆን ከመብቃቱም በላይ ይህንኑ እውን የሚያደርግ ፕሮግራም ይዞላችሁ ቀርቧል።
 
ውህድ ፓርቲያችን ሁሉንም ብሔሮች የሚያሳትፍና ከቀደመው አግላይ አካሄድ የምንማርበት፣ የሕዝብን ጥያቄ በተናበበ ሁኔታ የምንመልስበት፣ በፓርቲ ውስጥ መግባባትን በማጠናከር አጠቃላይ በአገራችን ብሔራዊ መግባባትን ለማምጣት የሚያስችለን በመሆኑ ህብረ ብሄራዊ ፌዴራላዊ ስርዓት እውን የሚሆንባት፣ የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት በምናደረገው ርብርብ ሁሉ ድጋፋችሁ እንደማይለየው ፓርቲያችን ርግጠኛ ነው።
 
በመሆኑም ብዝሃነታችንን ጠብቀን ለበለፀገች ኢትዮጵያ ግንባታ እጅ ለእጅ ተያይዘን እንድንሰራ ጥሪ እናስተላልፍላችኋለን።
የኢሕአዴግ ምክር ቤት
ህዳር 12 ቀን 2012 ዓ.ም
አዲስ አበባ
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም