ኢትዮጵያና ሱዳን የኢኮኖሚ ግንኙነታቸውን ማጠናከር እንደሚገባቸው ተገለጸ

76
ህዳር 12/2012 ኢትዮጵያና ሱዳን እንደ ህዝብ ለህዝብ ግንኙነታቸው ሁሉ የኢኮኖሚ ግንኙነታቸውን ማጠናከር እንደሚገባቸው ተገለጸ። ለሶስት ቀናት በኢትዮጵያ ጉብኝት ለማድረግ ትናንት ማምሻውን አዲስ አበባ የገባው የሱዳን ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ከኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ጋር ዛሬ ተወያይቷል። የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያና ሱዳን ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ታሪካዊና ባህላዊ መሰረት አለው። ኢትዮጵያና ሱዳን እንደህዝብ ለህዝብ ግንኙነታቸው የኢኮኖሚ ትስስራቸውን ለማጠናከር መስራት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል። በአገሮቹ መካከል ያለውን የአየር ትራንስፖርት ትስስር በመጠቀም የንግድ ግንኙነቱን ማሳደግ ተገቢ መሆኑንም ተናግረዋል። ሱዳን የሽግግር መንግስት ለመመስረት የሄደችበት መንገድ የሱዳን ህዝብ ተወያይቶ የራሱን ችግር መፍታት እንደሚችል ለዓለም ያሳያበት መሆኑን ነው ያመለከቱት። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው በበኩላቸው፤ የሱዳን ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ጉብኝት የአገሮቹን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ጠቁመዋል። በውይይቱ ወቅት የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ሱዳንን እንዲጎበኝ የሱዳን ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ጥሪ እንዳቀረበም ገልጸዋል። የሱዳን ፐብሊክ ዲፕሎማሲ በኢትዮጵያ በሚኖረው ቆይታ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ማጠናከር የሚያስችሉ ውይይቶችን ከተለያዩ አካላት ጋር እንደሚያደርግ አመልክተዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም